ካፍ ጋቦን ለምታስተናግድው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የአምስተኛ መርሃ ግብር የሚደረጉበትን ቀን ይፋ አድርጓል፡፡ በምድብ አስር ከአልጀሪያ፣ ሌሴቶ እና ሲሸልስ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ ቀጣይ ጨዋታን ማሴሩ ላይ ሌሴቶን የምትገጥም ይሆናል፡፡
ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከዋልያዎቹ መለያየት በኃላ ሃላፊነቱን የተረከቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሌሴቶ ጋር ዕሁድ ግንቦት 28 በማሴሩ ያደርጋሉ፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የጠበበ ዕድል ያለው ብሄራዊ ቡድናችን በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡
በምድቡ ሌላ ጨዋታ አልጄሪያ ቪክቶሪያ ላይ ከሲሸልስ ሐሙስ ግንቦት 25 ይደረጋል፡፡ የምድቡ መሪ አልጄሪያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከሲሸልስ ጋር ነጥብ መጋራት ብቻ በቂዋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምድብ መክፈቻ ጨዋታ ሌሴቶን ባህርዳር ላይ በጋቶች ፓኖም እና ሳላዲን ሰዒድ ግብ 2-1 ማሸነፋ ይታወሳል፡፡ ዋልያዎቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ጥሩ ሁለተኛ ሆኖ ለማለፍ የግዴታ ሁለቱን ቀሪ ጨዋታዎች ማሸነፍ እና የሌሎች ምድቦችን ውጤት መጠበቅ አለባቸው፡፡