የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገ ይጀመራል፡፡ ተቀራራቢ ነጥብ እና ከፍተና ፉክክር እስተናገደ በሚገኘው ምድብ ሀ ወልድያ ፣ፋሲል ከተማ እና መቐለ ከተማ ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዘው አንደኛውን ዙር አጠናቀዋል፡፡ የሶስቱ ክለቦች አሰልጣኞች ስለ ምድቡ ፉክክር ፣ ስለ ሁለተኛው ዙር እና ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
‹‹በሁለተኛው ዙር እስከ 5 ከሚገኙት ክለቦች ጋር በሜዳችን መጫወታችን ተጠቃሚ ያደርገናል›› ንጉሴ ደስታ – ወልድያ
የምድቡ ሁኔታ እና ፉክክር
‹‹ ከሁለቱ ምድቦች ጠንካራ ቡድኖች የሚገኙበት ምድብ ይህ ነው። በአንደኛው ዙር ከማያቸው ቡድኖች ፣ ከሚመዘገቡት ውጤቶች እና ከወቅታዊ አቋም አንፃር ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ፉክክር ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙርም ከዚህ በበለጠ ፉክክር ይጠበቃል። የውድድር ቀላል ባይኖርም በተለይ በዞናችን ከሚገኙት ስድስት ቡድኖች ጋር ያለው የደርቢነት ስሜት ከፍተኛ በመሆኑ የሚጠብቀን ጨዋታ ጠንካራ ይሆናል፡፡ ››
የአንደኛውን ዙር ደረጃ ስለማስጠበቅ
ቅድም እንዳልኩት በአንደኛው ዙር ላይ የነበረው ጠንከራ ፉክክር አሁንም እንደሚያጋጥመን እንጠብቃለን፡፡ ባለን የተጨዋቾች ጥራት ፣ በስታፉ ጥንካሬ እና በከተማ መስተዳድሩ ጥረት ጠንካራ ቡድን ሰርተናል፡፡ እንደዛም ቢሆን አጥቂና አማካይ ላይ ያሉብንን ክፍተቶች በጥልቀት ገምግመን ለክለቡ ይመጥናሉ ፣ በፍጥነት ከቡድኑ ጋር ተዋህደው ይጠቅሙናል ያልናቸውን ተጨዋቾች (ከሆሳህና ሀፍቶም ገ/እግዚአብሄር ፣ ከመድን ያሬድ ፣ ከድሬደዋ ከተማ በድሩ) አካተናል፡፡ በሜዳችንም ከሜዳችን ውጭም ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል። የህዝቡ ስሜትና ድጋፍ አስደናቂ ነው፡፡ ጨዋታ ባለን ቁጥር ሕዝቡ ከቤቱ ነቅሎ ወጥቶ ነው የሚደግፈን፡፡ የልምምድ ሜዳ ሳይቀር እየመጡ ነው የሚያበረታቱን፡፡ ስለዚህ እነሱንም ለማስደሰት ጠንክረን እንሰራለን››
የነጥብ መቀራረብና የመድን እና አማራ ውሃ ስራ ቀስ በቀስ መጠጋት…
‹‹ቡድኖች በእንደዚህ አይነት መንገድ እየተጠጉ ሲመጡ ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት እንድትሰጥ ያደርግሀል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ከሚገኙት ጋር የምንጫወተው በሜዳችን የምናገኛቸው በመሆኑ እነርሱን ለማምለጥ እንሰራለን። ከፍተኛ ትኩረት አድርገን የሕዝቡን ፍላጎት እናሳካለን ። ››
ስለ አዲሱ ሼይክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም?
‹‹ በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ሀገሮችን ስታድየሞች ተመልክቻለው፡፡ እንዲህ አይነት ስቴዲዮም አላየሁም ። ሁሉነገሩ የለሟላለት ሜዳ ነው። በዚህ ውብ ስቴዲዮም የምንጫወትበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ በቅርብ ቀን ይመረቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ››
‹‹ በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው›› ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ፋሲል ከተማ
የመጀመርያው ዙር…
‹‹ የ1ኛው ዙር ፉክክር በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ከአንድ እስከ አምስት ያሉት ቡድኖች ነጥባቸው ተቀራራቢ ነው፡፡ የክለቦቹም አቅም ተመጣጣኝ በመሆኑ ፍክክሩ ጥሩ ነበር። ሁለተኛው ዙርም ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀን ጥርጥር የለውም››
በሁለተኛው ዙር. . .
‹‹ በተወሰኑ ክፍተቶቻችን ላይ ተጫዋቾች ለመጨመር ሞክረናል፡፡ አምና ጅማ አባቡና የነበረው ተከላካዩ ምንያህልን እንዲሁም ገዛኸኝን ከአማራ ውሃ ስራ አምጥተናል፡፡ ራሳችንን አጠናክረን ጥሩ ስራ እንሰራለን ብለን እናስባለን፡፡››
ከመሪው እና ከተከታዮቻቸው ጋር ያላቸው ተቀራራቢ የነጥብ ልዩነት..
‹‹ይህን ምድብ ልዩ የሚያደርገው የነጥብ መቀራረቡ ነው፡፡ ከፊት ያሉትን ብቻ ሳይሆን ከኋላ ያሉትንም በንቃት የምንጠብቅበት ውድድር ነው፡፡ እያንዳንዱ ጨዋታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በመሆኑ በትኩረት ውድድር የምናደርግበት ይሆናል››
‹‹በ1ኛው ዙር ከሜዳችን ውጪ ውጤታማ ነበርን፡፡ በሁለተኛው ዙር የሜዳችንን ሪከርድ ለማሻሸል እንሰራለን›› ይድነቃቸው – መቐለ ከተማ
የ1ኛው ዙር ፉክክር
‹‹ ውድድሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በተለይ እኛ ያለንበት ምድብ ፕሪሚየር ሊጉን የሚያውቁ 5 ክለቦች ያሉበት መሆኑ ፣ የፋይናስ አቅማቸው የተደራጀ ቡድኖች ያሉበት መሆኑ፣ በፕሪሚየር ሊጉ ተጫውተው ያለፉ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች የሚገኙበት ቡድኖች ያሉበት መሆኑ ፉክክሩ ከሁለተኛው ምድብ ይልቅ የኛ ምድብ ከባድ ነው ። ከፕሪሚየር ሊጉ ያልተናነሰ ፉክክር ያለበት ምድብ ነው። ››
በሁለተኛው ዙር…
‹‹ በ1ኛው ዙር የነበሩብንን ጠንካራና ደካማ ጉን አይተናል፡፡ ያሉብን ክፍተቶች ለመድፈንና በየቦታው ያሉብንን ችግሮች ለማስተካከል ተጨዋቾችን አስፈርመናል፡፡ ጠንካራ ቡድን ሆነን እንቀርባለን››
በሁለተኛው ዙር ከመሪዎቹም ሆነ ከተከታዮቻችን የሚመጣውን ለመቋቋም ተዘጋጅተናል ። በእኛ በኩል በአንደኛው ዙር ከሜዳ ውጭ ጥሩ ነበርን፡፡ በሜዳችን ላይ ማግኝት የሚገባን ውጤት ለማግኝት ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ህዝቡም እኛን እየደገፈ በመሆኑ ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ነን፡፡ ስለሆነም ጥሩ ውጤት እናመጣለን። ››
———–
(የምድብ ለ ሶስት ክለብ አሰልጣኞችን አስተያየት ነገ ጠዋት እናቀርባለን)