የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ዋና አሰልጣኙ እየተዘጋጀ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ዋና አሰልጣኙ እየተዘጋጀ ነው

በሀዋሳ ከተማ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለፉትን አምስት ቀናት ያለ ያለ ዋና አሰልጣኙ ልምምድ እየሠራ ነው።

መስከረም አጋማሽ ላይ ከሱዳን እና ከሴኔጋል ጋር በቀናት ልዩነት ለሚጠብቀው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ከጀመረ አራት ሳምንታት አስቆጥሯል።

ወደ መጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ በደረሰው በዚህ ጊዜ የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ያለፉትን አምስት ቀናት ቡድኑ እያዘጋጁ አይደለም። ያለፉትን አራት ቀናት በድሬዳዋ በነበራቸው ቆይታ ሀገርን ወክለው በአፍሪካ መድረክ እየተሳተፉ የነበሩት የሲዳማ ቡና እና የወልዋሎ ዓ/ዩ ጨዋታዎችን የታደሙ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 18ኛ መደበኛ የምርጫ ጠቅለላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ተመልክተናል። ያለ ዋና አሰልጣኙ ያለፉትን አምስት ቀናት እየተዘጋጀ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሁን ሰዓት በሀዋሳ ሜዳ በምክትሎቹ እየተመራ ልምምድ እያደረገ ይገኛል።

በሌላ ዜና ለክለባቸው በአፍሪካ መድረክ ዝግጅት እና ጨዋታ ላይ የከረሙት የሲዳማ ቡና እና ከወልዋሎ ሰባት ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ በቀረበላቸው መሠረት ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቡድኑን ያልተቀላቀሉ መሆናቸውን ያረጋገጥን ሲሆን ዛሬ አስር ሰዓት ከአዲስ አበባ በመነሳት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።