የኢትዮጵያ እና ሞሮኮን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታወቁ

የኢትዮጵያ እና ሞሮኮን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታወቁ

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር የሚያደርጋቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በማጣሪያው የመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ራሷን ያገለለችውን ዩጋንዳን በፎርፌ አሸንፎ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉ ይታወሳል።

በማጣሪያው ሁለተኛ ዙር ሞሮኮን ለመግጠም በዝግጅት ላይ የሚገኘው እና በዛሬው ዕለት የመጀመሪያውን ጨዋታ ወደ የሚያደርግበት ድሬዳዋ ከተማ የገባው በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው ብሔራዊ ቡድናችን በዕለተ ሐሙስ ሕዳር 3 በድሬዳዋ ስታድየም፤ ማክሰኞ ሕዳር 11 ደግሞ በሞሮኮ ራባት ከተማ በሚገኘው ሞውላይ አል ሐሰን ስታድየም ጨዋታዎቹን የሚያከናውን ሲሆን ሁለቱም የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚመሩ ዳኞችም ታውቀዋል።

የመጀመሪያው በድሬዳዋ ስታዲየም የሚከናወነው ጨዋታ የማዳጋስካር ዜግነት ያላቸው ዳኞች የሚመሩት ሲሆን አንድሪያሳራ አርናድ ዛፊማሃቶሃ በዋና ዳኝነት፤ ላሬንዮን ሚላዴራ እና ራቮቪ ሃሲኖሮ ፊቲያቫና ደግሞ በረዳትነት ጨዋታውን ለመምራት ተመድበዋል።

በሞውላይ አል ሐሰን ስታድየም የሚደረገው የመልስ ጨዋታ ደግሞ ናይጄሪያዊው ዳኛ አቡበከር አብደላህ በዋና ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን የሀገሩ ልጆች አሕመድ ቲጃኒ ሙስጠፋ እና ቴጂሪ ቤስማርት ዲግቦሪም በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል።