ፕሪሚየር ሊግ ፡ ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች አዳማ ፣ መከላከያ እና ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ 20ኛ ሳምንት 3 ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ አዳማ ከተማ ፣ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ባለድል ሆነዋል፡፡

PicsArt_1463509476773

የዋና አሰልጣኙ እና ረዳቱ ፍልሚያ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሸሙት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ረዳታቸው ተደርገው በገብረመድህን የተሸሙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው  የሚመሯቸው መከላከያ እና ሲዳማ ቡና 09፡00 ላይ ተገናኝተው ጦሩ 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡  የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት እና ጥቂት ተመልካች በታደመበት ጨዋታ የመከላከያን የድ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ባዬ ገዛኸኝ በ44ኛው ደቂቃ ነው፡፡

PicsArt_1463509151294

ውዝግብና ሽኩቻ በበዛበት ጨዋታ አዳማ ሀዋሳን 3-0 አሸንፏል

አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 3-0 አሸንፏል፡፡ ሚካኤል ጆርጅ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ በ9ኛው ደቂቃ አዳማን ቀዳሚ ሲያደርግ ከእረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ ሱሌማን መሃመድ ከማዕዘን አካባቢ ያሻገረው ኳስ የሀዋሳው ግብ ጠበቂ ካሪያን ቴቤጎ ስህተት ታክሎበት የአዳማ ሁለተኛ ጎል ሆና ተመዝግባለች፡፡ የማሳረጊያውን ጎል  ደግሞ 84ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲካ አስፋው ከማእዘን የተሻገረውን ኳስ በግባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል፡፡

ጨዋታው ከጀመረበት ሰአት ጀምሮ ስፖርታዊ ጨዋነት በጎደለው ሁኔታ ከኳስ ጋር እና ኳስ ውጪ በሚፈጠሩ የተጨዋቾች ፀብ ምክንያት  በተደጋጋሚ ጨዋታው የተቋረጠ ሲሆን አሰልጣኞችም በተደጋጋሚ ተጫዋቾችን ለማረጋጋት ሜዳ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡ በተለይም ፋሲካ አስፋው እና ግርማ በቀለ ያሳዩት የነበረውን ያልተገባ ድርጊትን የዕለቱ ዳኛ በዝምታ ማለፋቸው ግርምትን አጭሯል፡፡

PicsArt_1463509557734

ኤሌክትሪክ ወሳኙን ጨዋታ አሸንፏል

በወራጅነት ስጋት ውስጥ የሚገኙትን ኤሌክትሪክ እና ዳሽን ቢራን ያገናኘው ወሳኝ ጨዋታ በኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ዳሽን ቢራ በ8ኛው ደቂቃ በቀድሞው የኤሌክትሪክ አምበል አስራት መገርሳ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግብ ቢመሩም ናይጄርያዊው ፒተር ኑዋዲኬ በ39ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ በ72ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም ከዳሽን ቢራ ተከላካዮች በማምለጥ ኤሌክትሪክን መሪ ሲያደርግ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪው ደቂቃ አዲ ነጋሽ ከዳሽን ተከላካዮች የነጠቀውን ኳስ በደረጄ አለሙ አናት ሰዶ የኤሌክትሪክን 3ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች እኩል 22 ነጥብ በመያዝ 11ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዥ

PicsArt_1463509407099

ከፍተኛ ግብ አግቢዎች

PicsArt_1463509196038

የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ደደቢት 09፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡ 11፡30 ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ድሬዳዋ ከተማ ይፋለማሉ፡፡ በ10፡00 አበበ ቢቂላ ላ ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭን ሲያስተናገድ ፣ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *