የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከጋና ለሚያደርገው ጨዋታ በተቃረበበት ወቅት 11 ተጫዋቾችን በመቀነስ 5 ተጫዋቾችን ጠርቷል፡፡
ቡድኑ ከግንቦት ሁለት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል በመሰባሰብ በልምምድ እና የዝግጅት ጨዋታዎች በማድረግ ቆይቶ በ11ኛው ሰአት በስብስቡ ላይ ጉልህ ለውጥ ማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ከ29 ተጫዋቾች ስብስብ መካከል የደደቢቱ ያሬድ ብርሃኑ ፣ የአዳማው ሱራፌል ዳኛቸው ፣ የወላይታ ድቻዎቹ ዳግም ንጉሴ እና ፈቱዲን ጀማል ፣ የሰበታው ኢብራሂም ሁሴን ፣ የሻሸመኔው ጫላ አስረስ ፣ የሙገሩ ክንዳለም ፍቃዱ ፣ የባንኩ ኤፍሬም ፣ የደቡብ ፖሊሱ ምስጋና ፣ የሀዋሳ ከተማው ደስታ ዮሃንስ የተቀነሱ ሲሆን የተሰጠው ምክንያትም በጉዳት እና አጥጋቢ እንቅስቃሴ ባለማሳየታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾቹ በተደረገላቸው የMRI ምርመራ እድሜያቸው ከ20 አመት በላይ በመሆናቸው እንደተቀነሱ ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ያመለክታል፡፡
አዲስ የተመረጡት 4 ተጫዋቾች ተመስገን አዳሙ (ሙገር ሲሚንቶ) ፣ ቢንያም አበራ (ደደቢት) ፣ ጋድ ጋትኮች (ጋምቤላ) ፣ ኩንአሩ ዋትዳል (ጋምቤላ) ናቸው፡፡ በሶማልያው የመጀመርያ ጨዋታ የተሰለፈው ተስፋዬ ሽብሩ ደግሞ ከጉዳት መልስ በድጋሚ ተጠርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ስብስቡ 23 ተጫዋቾችን ይዟል፡፡
በዛሬው የልምምድ ፕሮግራም 22 ተጫዋቾች ሲገኙ እርስ በእርስ ጨዋታ አድርገዋል፡፡ እጁ ላይ ጉዳት የደረሰበት አሜ መሃመድ በልምምዱ ላይ ያልተሳተፈ ተጫዋች ነው፡፡
ከ20 አመት በታች ቡድኑ ከሶማልያው ጨዋታ ዝግጅት ጀምሮ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ተጫዋቾችን ሲመርጥ እና ሲቀንስ የቆየ ሲሆን ከፌዴሬሽኑ የተሰጠው ትኩረትም ደካማ ይመስላል፡፡ ቡድኑ የልምምድ ማልያ ያልተሟላለት በመሆኑ በተለያየ ትጥቅ ልምምድ ለማድረግ ተገዷል፡፡
በሌላ በኩል ትላንት ምሽት በኢትዮዽያ ሆቴል ለ20 አመት በታች ቡድኑ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ከጋና ጋር በሚደረገው ጨዋታ ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡም ተጨማሪ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚጠብቃቸው ተገልፆላቸዋል፡፡