የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋናን 2-1 በረታበት ጨዋታ ሁለቱንም ግቦች በማስቆጠር ወሳኙን ሚና የተወጣው አሜ መሃመድ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ሁላችንም በሜዳችን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነበርን፤ በሙሉ የራስ መተማመን ነበር የተጫወትነው። ቡድኑም ጥሩ ነበር፤ ከጠበቅኩት በላይ ነው የተጫወትነው።”
ግብ ስለማስቆጠሩ
“እናንተም ስታናግሩኝ ግብ እንደማስቆጥር እርግጠኛ ሆኜ ነግሬያችሁ ነበር። (ከጨዋታው በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ግብ እንደሚያስቆጥር ተናግሮ ነበር) ጨዋታውም ቡዙም አልከበደኝም ነበር። ያልኩትም ተሳክቶ ሁለት ጎል በማግባቴ በጣም ደስ ብሎኛል።”
የአጥቂ ጥምረት
“በመጀመሪያው ግማሽ ከክለብ አጋሬ ከሱራፌል ጋር አብረን ነበር የተሰለፍነው። ሱራፌል ፈጣንና ለተከላካዮች አስቸጋሪ ተጫዋች መሆኑ ለእኔ ክፍተት ፈጥሮልኝ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ በብቸኛ አጥቂነት መሰለፌ እና ከጋናዎች የጉልበት ጨዋታ ራሴን ጠብቄ ለመጫወት መገደዴ እንደጨዋታው ጅማሬ የተሻለ እንዳልንቀሳቀስ አድርጎኛል።”
ስለ መልሱ ጨዋታ
“በመልሱ ጨዋታም የጋናዎች አጨዋወት ዛሬ ካየነው የተለየ አይሆንም። የእነርሱን ጨዋታዎች በቪዲዮ በማየታችን አጨዋወታቸውን እናውቀዋለን። እኛ መሃል ሜዳ ላይ ኳስ ይዘን የምንጫወት ከሆነ እዛም ሄደን እናሸንፋለን። ለአቻ ራሱ በፍፁም መጫወት የለብንም፤ በመልሱም ጨዋታ አሸንፈን ማለፍ ይገባናል። ስራዬ ስለሆነ ፈጣሪ ካለ በመልሱ ጨዋታም ግብ አስቆጥራለሁ ብዬ አስባለሁ።”