የ2016 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲጀመሩ የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ የግብፁ ዛማሌክ እና የኮትዲቯሩ አሴክ ሚሞሳ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮቹ ኤል ሜሪክ እና ያንግ አፍሪካንስ በሜዳቸው አቻ ተለያይተዋል፡፡
ማራካሽ ላይ ዋይዳድ ካዛብላንካ የአምና የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ላይ ጣፋጭ የሆነ የ2-0 ድል ተጎናፅፏል፡፡ የጨዋታ ብልጫ ለነበረው ዋይዳድ የድል ግቦቹን አቡድልላቲፍ ኑሰር እና ሬዳ ኤል ሃጆኦ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል፡፡ በውድድር ዓመቱ መልካም የሆነ አቋምን እያሳየ ለማይገኘው የሉቡምባሺዊ ክለብ የመልስ ጨዋታው ከወዲሁ ከባድ ሆኖበታል፡፡
ዳሬ ሰላም ላይ አል አሃሊን ያስተናገደው ያንግ አፍሪካንስ 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ጨርሰዋል፡፡ በፈርኦኖቹ አጥቂ አምር ጋማል አማካኝነት ግብ የማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰዱት አል አህሊዎች ሲሆኑ የቀድሞው የፊዮረንቲና እና ፔሩጂያ የመሃል ተከላካይ አህመድ ሄጋዚ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ያንግ አፍሪካንስ አቻ ሊለያይ ችሏል፡፡

አሴክ ሚሞሳን ለመግጠም ወደ አቢጃን የተጓዘው አል አሃሊ ትሪፖሊ የ2-0 ሽንፈትን ቀምሷል፡፡ ለአሴክ ሚሞሳ የድል ግቦቹን ዳኦ የሱፍ እና አካ ሰርጌ በሁለተኛው ኣጋማሽ አስቆጥረዋል፡፡
ዛማሌክ በፔትሮስፖርት ስታዲየም ኤምኦ ቤጃያን 2-0 አሸንፏል፡፡ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ጨዋታ መሃሙድ ካራባ እና አህመድ ሃሙዲ የዛማሌክን ሁለት ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ቤጃያ ተጫዋቾች ቀይ ካርድ የሚያሰጡ ከባድ ጥፋቶች ሲሰሩ የታዩ ሲሆን ከጨዋታው በኃላ የቤጃያ ክለብ አባላት የመሃል ዳኛውን በመክበብ ሲያዋክቡ ተስተውለዋል፡፡

የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ ባማኮ ላይ ያልተጠበቅ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ስታደ ማሊያንን 3-1 ከሜዳው ውጪ የረታው ዜስኮ ዩናይትድ ከ2009 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ምድብ ማጣሪው ለመግባት ከጫፍ ደርሷል፡፡ ምዋፔ ምዊልዋ እና ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ኢድሪስ ምቦምቦ ለዜስኮ አሸናፊነት ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡ ለማሊው ክለብ ሞሳኮዮ ዲያሎ በስሙ አስመዝግቧል፡፡
ኤል ሜሪክ ወደ ምድብ ማጣሪያው የሚያደርገውን ጉዞ አጨልሟል፡፡ ኦምዱሩማን ላይ የአልጄሪያውን ኢኤስ ሴቲፍ የገጠመው ሜሪክ 2-2 ተለያይቷል፡፡ ራጂ አብደል አቲ ሁለት ግቦችን ለሜሪክ ሲያስቆጥር በውድድሩ መልካም ብቃቱን እያሳየ ሚገኘው ማዕከላዊ አፍሪካዊው ኡደስ ዳጎሎ አንዲሁም አብዱልሞሜን ጃቦ አስቆጥረዋል፡፡
የቅዳሜ ውጤቶች
አሴክ ሚሞሳ (ኮትዲቯር) 2-0 አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)
ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 1-1 አል አሃሊ (ግብፅ)
ስታደ ማሊያን (ማሊ) 1-3 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)
ዋይዳድ ካዛብላንካ (ሞሮኮ) 2-0 ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ዛማሌክ (ግብፅ) 2-0 መውሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ)
ኤል ሜሪክ (ሱዳን) 2-2 ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ)