የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ የ2015 የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው የቱኒዚያው ኤቷል ደ ሳህል በናይጄሪያው ኢኒምባ ያልተጠበቀ ሽንፈትን ሲያስተናግድ የዲ.ሪ. ኮንጎው ቪታ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውን በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
ምፎን ኡዶ ኮከብ ሆነ በዋለበት ጨዋታ ኢኒምባ ዳግም ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ከጫፍ ደርሷል፡፡ በሜዳው ከፍተኛ ግምት ያገኘውን ኤቷል ደ ሳህልን ያስተናገደው ኢኒምባ በኡዶ ሶስት ግቦች 3-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኡዶ በቻምፒየንስ ሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች መጠን ወደ 7 በማሳደግ የኮከብ ግብ አግቢነቱን መምራት ጀምሯል፡፡ በእንግዶቹ በኩል ጋሃዚ አብልራዛቅ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በ71ኛው ደቂቃ ተወግዷል፡፡ ድሉ እየተዳከመ ለመጣው የናይጄሪያው ክለብ ዳግም ወደ ምድብ ማጣሪያው ለመግባት ለሚያደርገው ጥረት ወሳኝ ሲሆን ቱኒዚያ በምድብ ማጣሪያው ያለምንም ተወካይ የመቅረት ፈተና ተጋርጦባታል፡፡ የቱኒዚያው ሻምፒዮን ክለብ አፍሪካ በመውሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ ተሸንፎ በግዜ ከውድድር መሰናበቱ ይታወሳል፡፡
ኪንሻሳ ላይ ኤኤስ ቪታ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን 1-0 አሸንፏል፡፡ ኩል ምቦምቦ የቪታን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታዎች ከሳምንት በኃላ ይካሄዳሉ፡፡
የዛሬ ውጤቶች
ኢኒምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ) 3-0 ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ)
ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 1-0 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
Photo © Etole S De Sahle