ካንፌድሬሽን ካፕ፡ ኢኤንፒፒአይ ሲሸነፍ፤ አል አሃሊ ሸንዲ አቻ ወጥቷል 

የኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዕሁድ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ ወደ ጋቦን ያቀናው አኤንፒፒአይ በሲኤፍ ሞናና 2-0 ሲሸነፍ ሸንዲ ላይ የጋናውን ሚዲአማን ያስተናገደው አል አሃሊ ሸንዲ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ የታንዛኒያው አዛም የሁለት ግዜ የቻምፒየንስ ሊጉን አሸናፊን ኤስፔራንስን 2-1 ሲያሸንፍ የአንጎላው ሳግራዳ ኤስፔራንስ ከፖይት ኖይር በድል ተመልሷል፡፡

ሊበርቪል ላይ በተደረገ ጨዋታ የጋቦኑ ሲኤፍ ሞናና ኢኤንፒፒአይን 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኡመድ ኡኩሪ ተጠባባቂ ሆኖ በጀመረበት ጨዋታ ለባለሜዳዎቹ ሪክ ማርቴል አሎጎ ባ እንዲሁም ላምቤ ቢየሚ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል፡፡

አል አሃሊ ሸንዲ ከሚዲአማ ጋር 0-0 ተለያይቷል፡፡ በውድድሩ ላይ የቀረው ብቸኛው የሱዳን ተወካይ የሆነው ሸንዲ በተደጋጋሚ ወደ ሚዲአማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ ውጤቱ ጋናን በውድድሩ በብቸኝነት በመወከል ላይ በሚገኘው ሚዲአማ መልካም ሆኗል፡፡

በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ አዛም ከመመራት ተነስቶ ታላቁን የቱኒዚያ ክለብ ኤስፔራንስ ክለብን 2-1 አሸንፏል፡፡ የቱኒዙ ክለብ በሃይታም ጁኒ ግብ መምራት ቢችልም አዛሞች በረመዳን ሲንጋኖ እና ፋሪድ ሙሳ የሁለተኛ አጋማሽ ግቦች ሊያሸንፍ ችሏል፡፡ እራሱን በአዲስ መልክ እያደረጃ የሚገኘው ኤስፔራንስ አሁንም አዛምን ጥሎ የማለፍ ሰፊ ግምትን አግኝቷል፡፡

የኮንጎ ብራዛቪሉ ክለብ ቪታ ክለብ ሞካንዳ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት በሳግራዳ ኤስፔራንስ 2-1 ተሸንፏል፡፡ ለሳግራዳ የድል ግቦቹን የ37 ዓመቱ አርሰኒኦ ካቡንጉላ እና ሳሙኤል ዳ ሲልቫ ከመረብ አዋህደዋል፡፡

የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

የዕሁድ ውጤቶች፡

ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን) 2-0 ኢኤንፒፒአይ (ግብፅ)

አዛም (ታንዛኒያ) 2-1 ኤስፔራንስ ስፖቲቭ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)

አል አሃሊ ሸንዲ (ሱዳን) 0-0 ሚዲአማ (ጋና)

ቪታ ክለብ ሞናንዳ (ኮንጎ ብራዛቪል) 1-2 ሳግራዳ ኤስፔራንስ (አንጎላ)

 

Photo © ENPPI

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *