የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ የማጣሪያ ዙር የመልስ ጨዋታዎች ትላንት ሲጀመሩ የግብፁ ዛማሌክ፣ የአልጄሪያው ሴቲፍ እና የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባታቸውን ያረጋገጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ቤጃያ ላይ ዛማሌክ ከሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ ጋር 1-1 በመለያየት ወደ ምድብ ድልድሉ የገባበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በአመዛኙ ጥብቅ እና የተደራጀ የመከላከል አጨዋወትን ይዘው ወደ ሜዳ የገቡት ዛማሌኮች በቤጃያ ፍፁም የሆነ የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ያላቸው የካበት ልምድ ቤጃያን ጥለው ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ረድቷቸዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የዛማሌክ ግብ ጠባቂ አህመድ ኤል ሽናዊ ሲጎዳ ተቀይሮ የገባው መሃሙድ ጋንሽ መልካም እንቅስቃሴን አድርጓል፡፡
ቤጃያ በያያ ፋውዚ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ መምራት ቢችልም አህመድ ሃሙዲ ጨዋታውን ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ዛማሌክን አቻ አድርጓል፡፡ የካይሮው ክለብ ከ2014 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ምድብ አልፏል፡፡
የምስራቅ አፍሪካው ተወካይ ኤል-ሜሪክ ሴቲፍ ላይ ከኢኤስ ሴቲፍ ጋር ያለግብ ጨዋታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ከኦምዱሩማኑ ጨዋታ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለው ሜሪክ የአጥቂዎች የአጨራረስ ድክመት ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ድልድል እንዳይገባ አድርጓታል፡፡
የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ የማሊውን ስታደ ማሊያን በሜዳው 2-1 በማሸነፍ ከ2009 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ምድብ ድልድሉ ማለፍ ችሏል፡፡ የዜስኮን የድል ግቦች በዓመቱ መጀመሪያ የኬንያው ተስካርን ለቆ ክለቡን የተቀላቀለው አጥቂው ጄሲ ዌሬ እና ሜይቢን ሙዋባ ከመረብ ሲያዋህዱ ሙሳ ኩሊባሊ የባማኮውን ክለብ ግብ ማስገኘት ችሏል፡፡
ወደ ምድብ ድልድሉ ማለፍ ያልቻሉት መውሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ፣ ኤል-ሜሪክ አና ስታደ ማሊያን ወደ ኮንፌድሬሽን ካፕ ሶስተኛ የማጣሪያ ዙር በቀጥታ የሚገቡ ይሆናል፡፡
የማክሰኞ ውጤቶች፡
ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) 1-1 ዛማሌክ (ግብፅ) [1-3]
ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) 2-1 ስታደ ማሊያን (ማሊ) [5-2]
ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ) 0-0 ኤል-ሜሪክ (ሱዳን) [2-2]
የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡ የዓምና ሻምፒዮኑ ቲፒ ማዜምቤ ከ2013 በኃላ ከምድብ ማጣሪያ ውጪ ላለመሆን በማለም የሞሮኮውን ዋይዳድ ካዛብላንካን ይገጥማል፡፡ ዋይዳድ በመጀመሪያው ጨዋታ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በውድድሩ ላይ የቀረው ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስ የግብፁን አል አሃሊን አሌክስንደሪያ ላይ ይገጥማል፡፡ ዳሬ ሰላም ላይ 1 አቻ የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ የአሃሊ ደጋፊዎች እንዲታደሙ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
አሴክ ሚሞሳስ ቱኒዚያ ላይ ከአሃሊ ትሪፖሊ ጋር ይጫወታል፡፡ አቢጃን ላይ 2-0 ያሸነፈው አሴክ ወደ ምድብ ድልድሉ የመግባት ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡
ኤቷል ደ ሳህል በኢኒምባ የደረሰበት የ3-0 ሽንፈት ለመቀልበስ ይጫወታል፡፡ የኢኒየምባ ክለብ አባላት ቱኒዚያ ላይ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ አይደሉም፡፡ ክለቡ እንዳስታወቀው ከሆነ ከካፍ ህግ ውጪ አስተናጋጁ ኤቷል በደል አድርሷባቸዋል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውን ቪታ ክለብን የሚያስተናግድበት ሌላው የሚጠበቅ ጨዋታ ነው፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች፡
15፡30 – ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) [0-2] ስታደ ቲፒ ማዜምቤ
16፡00 – አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) ከ አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) [0-2] ስታደ ቸድሊ ዞዊተን
19፡00 – ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ ኢኒምባ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ) [0-3] ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ
19፡30 – ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) ከ ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) [0-1] ሉካስ ማስተርፒስ ሞርፒ ስታዲየም
19፡30 – አል አሃሊ (ግብፅ) ከ ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) [1-1] ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም