ትላንት በሶስት የአፍሪካ ከተሞች በተካሄዱ የ2016 ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፍ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ዙር የመልስ ጨዋታዎች የቱኒዚያዎቹ ስታደ ጋብሲየን እና ኤስፔራንስ እንዲሁም የአንጎላው ሳግራዳ ኤስፔራንሳ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ሶስተኛው የማጣሪያ ዙር ማለፍ ችለዋል፡፡
ስታደ ጋብሲየን የዛምቢያውን ዜናኮን 3-0 መርታት ችሏል፡፡ የስታደ ጋብሲየንን የድል ግቦች አህመድ ሆስኒ እና ሂቸም ኢሲፊ (2) በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡
ቱኒዝ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ተወካዩን አዛምን ያሸነፈው ኤስፔራንስ ሶስተኛውን የማጣሪያ ዙር የተቀላቀለ ሌላኛው የቱኒዚያ ክለብ ሆኗል፡፡ የመጀመሪያውን አጋማሽ በጠንካራ መከላከል የአጠቃላይ መሪነታቸውን ማስጠበቅ የቻሉት አዛሞች በሁለተኛው አጋማሽ በትኩረት ማነስ እና የግብ ጠባቂ ስህተት ምክንያት በተቆጠሩባቸው ሶስት ግቦች ተሸንፈው ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡ ሳአድ በጉኢር፣ ሃይታም ጆኦኒ እና ፋክረዲን ቤን የሱፍ የኤስፔራንስ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡
የአንጎላው ሳግራዳ ኤስፔራንሳ ዳግም ቪታ ክለብ ሞካንዳን አሸንፏል፡፡ ሳግራዳ 2-0 በማሸነፍ ነው ወደ ተከታዩ ዙር የሚያሳልፈውን ትኬት የቆረጠው፡፡
የሁለተኛ ዙር የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊዎች በሶስተኛው ዙር ወደ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ማጣሪያ መግባት ካልቻሉ ክለቦች ጋር ተፋልመው ወደ ምድብ ማጣሪያ የሚገቡ ይሆናል፡፡
የማክሰኞ ውጤቶች፡
ስታደ ጋብሲየን (ቱኒዚያ) 3-0 ዛናኮ (ዛማቢያ) (4-1)
ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) 3-0 አዛም (ታንዛኒያ) (4-2)
ሳግራዳ ኤስፔራንሳ (አንጎላ) 2-0 ቪታ ክለብ ሞካንዳ (ኮንጎ ብራዛቪል) (4-1)
የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ የአዲስ ህንፃው አል አሃሊ ሸንዲ ከጋናው ሚዲአማ ጋር ይጫወታል፡፡ ለጨዋታው ቀደም ብሎ ወደ ጋና ያቀናው ሸንዲ በመጀመሪያ ዙር ያስመዘገበውን ውጤት ለማስተካከል ሚዲአማን ይገጥማል፡፡
አሰልጣኙ ሃምዳ ሰድኪን ባሳለፍነው ሳምንት ያሰናበተው ኢኤንፒፒአይ በሜዳው የጋቦኑን ሞናናን ያስተናግዳል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ 2-0 የተሸነፈው እና በጥሩ አቋም ላይ ለማይገኘው ኢኤንፒፒአይ ውጤቱን ለመቀልበስ አስቸጋሪ ይሆንበታል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ሞናናን በሚገጥመው ቡድን ውስጥ ተካቷል፡፡
የሞሮኮው ካውካብ ማራካሽ በሜዳው ሞሊዲያ ክለብ ኦራን እንዲሁም ምስር ኤል ማቃሳ ሲኤስ ኮንስታንታይን የሚያስተናግዱበት የሰሜን አፍሪካ ደርቢ ጨዋታዎች ከሚጠበቁት ጨዋታዎች መካከል ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ የማለፍ ተስፋው የጨለመው የዩጋንዳው ቪላ ኤፍዩኤስ ራባትን ካምፓላ ላይ ይገጥማል፡፡ ራባት ላይ 7-0 የተሸነፈው ቪላ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፉ ነገር ያበቃለት ይመስላል፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች፡
15፡00 – ሚዲአማ (ጋና) ከ አል አሃሊ ሸንዲ (ሱዳን) (0-0) ኢሲፖንግ ስፖርትስ ስታዲየም
16፡00 – ስፖርት ክለብ ቪላ (ዩጋንዳ) ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) (0-7) ማንዴላ ናሽናል ስታዲየም
18፡00 – ኢኤንፒፒአይ (ግብፅ) ከ ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን (0-2) ፔትሮ ስፖርት ስታዲየም
18፡00 – ምስር ኤል ማቃሳ (ግብፅ) ከ ክለብ ስፖርቲፍ ኮንስታንታይን (አልጄሪያ) (0-1) ፋዩም ስታዲየም
20፡00 – ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) ከ ሞሊዲያ ክለብ ደ ኦራን (አልጄሪያ) (0-0) ግራድ ስታደ ማራካሽ