ቻምፒየንስ ሊግ፡ ቲፒ ማዜምቤ እና ኤቷል ደ ሳህል ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ ሆነዋል 

የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቋል፡፡ የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ የአምና አሸናፊውን ቲፒ ማዜምቤን ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ ሲያደርግ የአምና የኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ደ ሳህል በኢኒምባ በመለያ ምት ተሸንፎ ወደ ምድብ ሳይገባ ቀርቷል፡፡ አል አሃሊ በባከነ ሰዓት በተቆጠረ ግብ ያንግ አፍሪካንስ ሲያሸንፍ ቱኒዚያ ላይ በአሃሊ ትሪፖሊ የተሸነፈው አሴክ ሚሞሳስ ከ8 ዓመት በኃላ ወደ ምድብ ማጣሪያው ማለፍ ችሏል፡፡

በስታደ ቲፒ ማዜምቤ የተደረገው የቲፒ ማዜምቤ እና የዋይዳድ ካዛብላንካ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ በጨዋታው ላይ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ማዜምቤዎች በተከላካዩ ሳሊፍ ኩሊባሊ ግብ መምራት ቢችሉም ሬዳ ሃጆሆ የካዛብላንካው ክለብ ወደ ምድብ ማጣሪያ የወሰደውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ማዜምቤ ከ2013 በኃላ ወደ ምድብ ድልድል መግባት ሲያቅተው ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡

PicsArt_1461220265042

ሶስ ላይ ኤቷል ደ ሳህል በአስገራሚ መልኩ በኢኒምባ ፖርት ሃርኮት ላይ የደረሰበትን የ3-0 ሽንፈት ቢቀለብስም በመለያ ምት በ2005ቱ የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ተሸንፎ ከቻምፒየንስ ሊጉ ተሰናብቷል፡፡ መጎሻሸሞች፣ ጥፋቶች እና የዳኛ ፊሽካ በበዛበት ጨዋታ ኤቷል በሃምዛ ላሃማር እና በብራዚላዊው አጥቂ ዲዮጎ አኮስታ (2) ግብ 3-0 ማሸነፍ ቢችልም አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው መለያ ምት ኢኒምባ 4-3 በማሸበፍ ምድብ ማጣሪያውን ተቀላቅሏል፡፡

አል አሃሊ ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስን 2-1 አሸንፏል፡፡ ለአሃሊ የድል ግቦቹን የቀድሞ የቶትንሃም ተጫዋች ሆሳም ጋሃሊ እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ የሰከንዶች ግዜ ሲቀሩት አብደላ ኤል ሰዒድ አስገኝተዋል፡፡ ለያንጋ ዶናልድ ንጎማ ማስቆጠር ችሏል፡፡

PicsArt_1461220340290

ቪታ ክለብ በማሜሎዲ ሰንዳውንስ እንዲሁም አሴክ ሚሞሳ በአሃሊ ትሪፖሊ በተመሳሳይ 2-1 በሆነ ውጤት ቢሸነፉም ወደ ምድብ ከማለፍ ያገዳቸው ነገር የለም፡፡ ታቦ ንቴቴ በፍፁም ቅጣት ምት እና ቲቦጎ ላንገርማን ለሰንዳውን ማስቆጠር ሲችሉ ኩሌ ሞቦምቦ ቪታ ወደ ምድብ ያሳለፈች ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ ማስቆጠር ችሏል፡፡ አሃሊ ትሪፖሊ አሴክ ሚሞሳን 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ለባለሜዳዎቹ ዛካሪያ ኢላፊ እና መሃመድ ፉአድ በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥሩ ዛካሪ ያኒክ የአሴክን ወደ ምድብ ከስምንት አመታት በኃላ ማለፍ ያረጋገጠች ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡

በሁለተኛ ዙር ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ የሆኑት ስምንት ክለቦች በቀጥታ ወደ ኮንፌድሬሽን ካፕ ሶስተኛ ዙር ያልፋሉ፡፡

በምድበ ማጣሪያው ውስጥ አራት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች የሚገኙ ሲሆን ግብፅ ሁለት ክለቦችን ወደ ምድብ በማሳለፍ ብቸኛዋ ሃገር ነች፡፡

 

ውጤቶች፡

ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ ኮንጎ) 1-1 ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ) (1-3)

አል አሃሊ (ግብፅ) 2-1 ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) (3-2)

አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) 2-1 ኤሰክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) (2-3)

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) 2-1 ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንኮ) (2-2)

ኤቷል ስፖርትቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 3-0 ኢኒምባ (ናይጄሪያ) (3-3 በመለያ ምት ኢኒምባ 4-3 አሸንፏል)

የምድብ ድልድሉን የተቀላቀሉ ስምንት ክለቦች

አል አሃሊ፣ ዛማሌክ፣ አሴክ ሚሞሳስ፣ ዜስኮ ዩናይትድ፣ ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ ኤኤስ ቪታ ክለብ፣ ኢኒምባ እና ኢኤስ ሴቲፍ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *