ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከሜዳቸው ውጪ ድል ሲያስመዘግቡ ዳሽን ቢራ በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ያጠናከረበትን ፣ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን ያሰሻለበትን ፣ ዳሽንቢራ ደግሞ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡

ዛሬ የካሄዱት ሁሉም ጨዋታዎች በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ለማሰብ በአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተጀምረዋል፡፡

PicsArt_1461262923053

ወደ ይርጋለም የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ቀጥሏል፡፡ ከአመታት ቆይታ በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመለሰው ሳላዲን ሰኢድ በ36ኛው ደቂቃ የፈረሰኞቹን ብቸኛ የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ውጤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተከታዩ አዳማ ከተማ በ6 ነጥቦች እንዲርቅ ሲያስችለው በሜዳው በተከታታይ የተሸነፈው ሲዳማን ቁልቁል እንዲሸራተት አድርጎታል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ለ2ኛ ጊዜ በያበን ዊልያም የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ታግዞ አሸንፏል፡፡ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች በተስተዋሉበት ጨዋታ ሁለት የቀይ ካርዶች በአወዛጋቢ የተመዘዙ ሲሆን በርካታ ቢጫ ካርዶችም ታይተዋል፡፡ በ57ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ክል ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ያቡን ዊልያም ወደ ግብነት ቀይሮ ለቡና 3 ነጥብ አስገኝቷል፡፡

ጎንደር ላይ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ 4-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል፡፡ የተሻ ግዛው የዳሽንን ቀዳሚ ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ ቶጓዊው አጥቂ ኤዶም ሆሶውሮቪ 3 ግቦች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡ የኤዶም ሐት-ትሪክ የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

PicsArt_1461263358672

ሃዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ረቷል፡፡ አስቻለው ታመነ በ5ኛው ደቂቃ ሀዋሳን ቀዳሚ ሲያደርግ ዘንድሮ በመልካም አቋም ላይ የሚገኘው ደስታ ዮሃንስ በ30ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል፡፡
ድሉ በተከታታይ ሶስተኛ ተከታታይ ጨዋታውን ያሸነፈው ሀዋሳን በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ማለቱን እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ውጤቱ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በርካታ ተጫዋቾችን ላዘዋወረው አርባምንጭ በወራጅ ስጋት ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡

PicsArt_1461262787077

11፡30 ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ኤሌክትሪክ 1-0 ተሸንፎ ወደ ወራጅ ቀጠናው ገብቷል፡፡ ታፈሰ ተስፋዬ የአዳማን የድል ግብ ሲያስቆጥር የግብ መጠኑንም 10 በማድረስ ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን መምራቱን ቀጥሏል፡፡
በጨዋታው ኤሌክትሪክ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ፒተር ኑዋድኬ መትቶ በጃፋር ደሊል ሲመለስበት ኤሌክትሪኮች ያስቆጠሩት ግብ ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ሳይፀድቅ መቅረቱ አወዛግቧል፡፡ አዳማ ድሉን ተከትሎ ነገ ጨዋታው ከሚያደርገው ደደቢት በ2 ነጥብ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የ15ኛ ሳምንት ቀሪ አንድ ጨዋታ ነገ ሲደረግ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደደቢት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዥ

PicsArt_1461262681122

ከፍተኛ ግብ አግቢዎች

PicsArt_1461262717909

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *