ለአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ጅቡቲ ላይ ሶማልያን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን 2-0 አሸንፏል፡፡
ከ15 ቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ 2-1 ያሸነፈው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የማሸነፍያውን ግብ ያስቆጠረው ተስፋዬ ሽብሩን ጨምሮ የ5 ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ካለግብ ወደ መልበሻ ክፍል ቢያመሩም በእንቅስቃሴ ረገድ ኢትዮጵያ የተሻለች እደነበረች የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ኦሜ ከቢንያም የተሸገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ ክልሉ ሲገባ የሶማልያ ተከላካይ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም በላይ ወደ ግብነት ቀይሮ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ሲያደርግ በ52ኛው ደቂቃ በንያም በላይ በረጅሙ ያሻገረው ኳስ የሶማልያ ተከላካች በአግባቡ ባለመቆጣጠራቸው ኦሜ መሃመድ አግኝቶ የኢትዮጵያን 2ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ግቦች ለማስቆጠር በዳዊት ፣ ዘሪሁን እና ደስታ አማካኝነት ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በአጠቃላይ በጨዋታው ኢትዮጵያ በኳስ ቁጥጥር የተሸለች ስትሆን ሶማልያዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክል ለመድረስ ጥረት አደርገዋል፡፡ የነበረው ከፍተኛ ሙቀት ለመጫወት አዳጋች የነበረ መሆኑም ታውቋል፡፡
ድሉ ኢትዮጵያን በድምር ውጤት 4-1 በማሸነፍ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ያሳለፋት ሲሆን በቀጣዩ ዙር በ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ገናና ስም ያላት ጋናን ትገጥማለች፡፡