ታክቲካዊ ዳሰሳ ፡ ደደቢት 0-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄዱ ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በገጠሙበት የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ንግድ ባንኮች በፊሊፕ ዳውዚ የመጀመሪያ አጋማሽ ጎል 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡ በጨዋታው ላይ የነበሩ ዋና ዋና ታክቲካዊ ጉዳዮችንም እንደተለመደው ሶከር ኢትዮጵያ ይዛላችሁ ቀርባለች፡፡

ከሳምንት በፊት በሁለተኛው ዙር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ከነበረው አሰላለፍ ላይ የተወሰኑ ለውጦች አድርጎ የገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትላንቱ ጨዋታ የተሻለ ተንቀሳቅሷል፡፡ የቡድኑ ዋና አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ ወደ ቋሚ አሰላለፍ መመለሱን ተከትሎ የኤፍሬም አሻሞና የፍቅርየሱስ ተክለብርሃንን ሚና ወደ መስመር አጥቂነት የቀየረው ቡድኑ በቡናው ጨዋታ ላይ ከተጠቀመበት የ4-1-4-1 አጨዋወት ወደ 4-3-3 መጥቷል፡፡ ሰለሞን ገ/መድህንና አብዱልከሪም መሀመድም ከሶስቱ አጥቂዎች ጀርባ የመሀል ሜዳ አማካይ የነበሩ ሲሆን ከነርሱ ኋላ እና ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ጋብርኤል የተከላካይ አማካይነት ኃላፊነት ነበረው፡፡

የያሬድ ዝናቡን መጎዳት ተከትሎ በተከላካዮች ፊት ያለው ቦታ ላይ ሳምሶን ጥላሁንን ከአዲሱ ጋናዊ ፈራሚ ክዌሲ ኬሊ ጋር በማጣመርና ከብቸኛው አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚ ጀርባ ወግደረስ ታዬን ሽመክት ጉግሳንና ብርሀኑ ቦጋለን በአማካይ ሚና በማሰለፍ ነበር ደደቢት ጨዋታውን የጀመረው፡፡ በዚህ መሰረት ጨዋታውን በ4-2-3-1 አቀራረብ የጀመረው ቡድኑ ሳምሶን ጥላሁንን ክዊሲ ኬሊ ፊት ባለው ቦታ ላይ ካሉት አማካዮች ጋር ቀርቦ የመጫወት ኃላፊነትም ሰጥቶት ታይቷል፡፡
image

የሁለቱም ቡድኖች ወደ መሀል አጥብቦ መጫወት

አብዛኛውን የጨዋታውን ክፍል በመሀል ሜዳው ላይ በሚደረጉ ፍትጊያዎችና ተደጋጋሚ ኳስ መነጣጠቆች መታጀቡ በጨዋታው ተደጋጋሚ የጐል ሙከራዎችን ለማየት አስቸጋሪ አድርጐት ታይቷል (ምስል 2 ቢጫው ክብ)፡፡

ከሁለቱ ቡድኖች በኳስ ቁጥጥር እና በአጠቃላይ በመሀል ሜዳው ላይ የተሻለ ብልጫ የነበረው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድን ሦስቱ አማካዮች በጨዋታው ላይ ኃላፊነታቸውን በተሻለ ታታሪነት ሲተገብሩ ታይተዋል፡፡ የአማካይ ተከላካዩ ጋብርኤል ኳስ የመንጠቅ እንዲሁም እራሱን ከደደቢት አማካዮች ጫና ነፃ እያረገ ኳስን ለመቀበል እና ማጥቃትን ለማስጀመር ይሞክር የነበረበት አኳኋን ተጨዋቹን የቡድኑ አንዱ ጠንካራ ጐን አድርጐት ነበር፡፡ ሁለቱ አማካዮች አብዱልከሪምና ሰለሞንም የማጥቃትና የመከላከል ኃላፊነታቸውን በተመጣጠነ መልኩ ሲወጡ ተስተውሏል፡፡  ይኸም ለቡድኑ የመሀል ሜዳ ጥንካሬ ወሳኝ ነበር፡፡ ከሰለሞን እና አብዱልከሪም እንቅስቃሴ በተጨማሪ በመስመር አጥቂነት በግራና በቀኝ የተሰለፉት ኤፍሬምና ፍቅረየሱስም በተለይ ቡድኑ በሚጠቃበት ወቅት ወደኋላ እየተመለሱ ለአማካይ ክፍሉ የቁጥር ብልጫ ሲሰጡት ነበር፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች ቡድኑ ወደ 4-1-4-1 የቀረበ ቅርፅ ይይዝ ነበር፡፡ የፊት አጥቂው ፊልፒ ዳውዝም ለቡድኑ ከፊት አስፈሪነትን ያላብሰው የነበረ ሲሆን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደግራ እየወጣ በኤፍሬም አሻሞ በኩል የሚመጡ ኳሶችን እየተቀበለ ይዞ ለመግባት ይሞክር የነበረበት አጨዋወት የደደቢት ተከላካዮችን ቅርፅ የሚያዛባ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፊሊፕ መሰለፍ ተከላካዮቹ  ደፍረው ወደ መሀል ሜዳው በመጠጋት በተደጋጋሚ በእነርሱ እና በአማካይ መስመሩ መካከል ሲፈጠር የነበረውን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብ እንዳይሞክሩ አድርጓቸው ነበር፡፡

እነዚህ ነጥቦች በንግድ ባንክ በኩል በመልካም ጎን የሚነሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በአብዛኛው ያጠቃበት የነበረው መንገድ እንደተጋጣሚው ሁሉ መሀል ለመሀል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የነበረ መሆኑ የመሀል ሜዳ ላይ ብልጫውን ወደ ብዙ የጐል ማግባት አጋጣሚዎች ለመቀየር አላስቻለውም፡፡ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች ኤፍሬም እና ፍቅረየሱስም የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም እና ጨዋታውን ወደጐን ከመለጠጥ ይልቅ ኳስን በሚያገኙባቸው የማጥቃት ሂደቶች ላይ  ወደ ወስጥ ለመግባት ያደርጉ የነበረው ጥረት የጐላ ነበር፡፡  ይህን ተከትሎም በሜዳው ግራና ቀኝ የሚተውቱን ክፍተትም የመስመር ተከላካዮቹ መጠቀም በሚገባቸው መጠን ሲጠቀሙበት አልተስተዋሉም (ምስል 2 ፡ ቀይ መስመሮች)፡፡

image-5ecc4fd04a76783f5d220c8bb8f29caaca12d87cf3f7ef7271c43c97dd499730-v.jpg

በዚህ ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍቅረየሱስ ጀርባ የተሰለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳንኤል አድሀኖም የማጥቃት ተሳትፎ በተሻለ መልኩ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከደደቢት ተከላካዮች ፊት ይፈጠር የነበረውን ሰፊ ክፍተትም መጠቀም በነበረበት ደረጃ ለመጠቀም አለመቻሉም ሌላው ደካማ ጐኑ ነበር፡፡ እንደ ኤፍሬም እና ፍቅረየሱስ አጥብቦ መጫወት እንዲሁም እንደ አብዱልከሪምና ሰለሞን እንቅስቃሴ ይህንን ደካማውን የደደቢትን ቦታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አብዝተው መጠቀም ነበረባቸው ነገር ግን ይህን አለማረጋቸው ተጨማሪ ጐሎችን ለማስቆጠር በቂ እድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ ቡድኑ መሪነቱን ለማስጠበቅ ባደረገው ጥረት ግን ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ወቅት የአማከዮቹና የመስመር አጥቂዎቹ ሚና ወሳኝ ነበር፡፡

የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ቡድን በዚህ መልክ እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ ቅርፁን እንደያዘ ቆይቶ  አብዱልከሪም በታዲዮስ ወልዴ(18) ተቀይሮ በወጣበት አጋጣሚ ወደ 4-2-3-1 አጨዋወት ተቀይሮ ታይቷል (ምስል 3) ፡፡  ታዲዮስ ከጋብርኤል ጐን በመሆንም ይበልጥ ቡድኑ ጐል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አስችሎታል፡፡

በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጎል ላይ በመድረስ እንዲሁም ከመስመር በተለይ ከቀኝ መስመር በሚነሱ አስፈሪ የማጥቃት አቀራረቡ የምናውቀው ደደቢት በትላንቱ ጨዋታ ይህን አስፈሪነቱን አጥቶት ነበር፡፡  ቡድኑ በተጋጣሚው የተወሰደበት የመሀል ሜዳ ብልጫ ለአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ኳስ የማቀበያ አማራጭም ለማግኘትም ሆነ ኳስን ለመቀበል እራሳቸውን ነፃ የሚያረጉበትን መንገድ ለማግኘት እንዲከብዳቸው አድርጎ ነበር፡፡ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የቡድኑ የአማካይ መስመር በእጅጉ ተፈትኗል፡፡ የፊት አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚም በቂ እድሎችን ሳያገኝ በንግድ ባንክ የመሀል ተከላካዮች መሀል ብዙ ጊዜውን አሳልፏል፡፡  የደደቢት የመሀል ክፍል ችግር መነሻ የነበረው ክዌሲ ኬሊ እና የወግደረስ እንቅስቃሴ ነበር፡፡  ክዌሲ ኬሊ በተለይ ከንግድ ባንክ የመሀል አማካዮች እንቅስቃሴ ጋር እየተሳበ ወደፊት ይሄድባቸው የነበሩ አጋጣሚዎች ከተከላካዮቹ ፊት በመሆን ለቡድኑ ሽፋን መስጠት በሚኖርባቸው ጊዜያት እና የተጋጣሚ ቡድን በሚያጠቃበት አጋጣሚ ከኳስ ጀርባ ይታይ ነበር፡፡  በዚህ ረገድ የተጨዋቹ እንቅስቃሴ በግልፅ ከቡድኑ ጋር ለመዋሀድ ገና እንደሆነ የሚያሳይ ነበር፡፡

የክዌሲ ደካማ እንቅስቃሴም ወደፊት በመሄድ እና ጫና በመፍጠር ይታወቅ የነበረውን የሳምሶን ጥላሁን አጨዋወትም ለመቀነሱ አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ ቡድኑ በሁለት አጥቂዎች ይጠቀም በነበረበት ጊዜ የመሀል ሜዳውን እንቅስቃሴ በመምራት ለአጥቂዎች ኳስ በማድረስ እንዲሁም ከመስመር አማካዮቹ ጋር ኳስን የመስጫና የመቀበያ አማራጭ በመፍጠር በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የነበረው ሳምሶን ትላንት የክዌሲነን ክፍተቶች ተከትሎ በአብዛኛው ይገኝበት የነበረው በራሱ በደደቢት የሜዳ ክፍል ላይ መሆኑ እንደቀደመው ጊዜ የማጥቃት አቅሙን መጠቀም እንዳይችል አድርጐታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከመስመር አማካዮቹ ብርሀኑ ና ሸመክት ጋርም የነበረውን ግንኙነት በጣሙን ቀንሶታል፡፡

በሌላ በኩል በሁለቱ የመስመር አማካዮች መካከል የተሰለፈው ወግደረስ ታዬ በቀላሉ በንግድ ባንክ አማካዮች ቁጥጥር ሥር ወድቆ ነበር፡፡  ተጨዋቹ በሜዳው ቁመት ሳምሶን ይንቀሳቀስ ከነበረበት ቦታ እስከ አጥቂው ሳሞኤል ሳኑሚ ድረስ ባለው ቦታ ብቻ ላይ ያተኮረ አጨዋወት ተፅዕኖውን ቀንሶት ታይቷል፡፡ የሄው የተደጋገመ እንቅስቃሴም ወግደረስ ከመስመር አማካዮቹ ጋር የነበረውን ግንኙነትም እንደዚሁ የተዳከመ እንዲሆን እና በተጋጣሚው አማካዮች በቀላሉ እንዲሸፈን እንዲሁም ተጨዋቹ በማጥቃቱ ላይ ሊኖረው ይገባ የነበረውን አስተዋጽዎ እንዳይተገብር አድርጎታል፡፡

በወግደረስ ግራና ቀኝ የተሰለፉት ብርሀኑ ቦጋለና ሽመክት ጉግሳ ሷስ በሚያገኙባቸው አጋጣሚዎች በአቅራቢያቸው ራሱን ነፃ አድርጎ የመጨረሻ የግብ እድሎችን ለመፍጠር በሚያስችለው ቦታ ላይ ሆኖ ኳስ የሚቀበላቸው ተጫዋች በማጣት  ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ወደ መሀል የሚያደርጉት እንቅሰቃሴ በተደጋጋሚ በንግድ ባንክ አማካዮች እና የመስመር ተከላካዮች ሲጨናገፍባቸው ነበር፡፡

ቡድኑ የተሻለ ክፍተት ሊያገኝ ይችልበት የነበረውን ሁለቱ የመስመር አማካዮች ትተውት ወደ ውስጥ ሲገቡ የሚፈጠረውን በሁለቱና ክንፎች ይታየ የነበረ የማጥቃት አማራጭ ክፍተትም  ለመጠቀም የመስመር ተከላካዮቹ የወደፊት እንቅስቃሴ በቂ አለመሆን ይህን አማራጭ እንዳይጠቀም አድርጎታል(ምስል 2 ቀይ መስመሮች) ፡፡

ባጠቃላይ የቡድኑ ወደመሀል የጠበበ የጥቃት  አካሄድ ለንግድ ባንክ ተጨዋቾች ለመቆጣጠር ከባድ አልነበረም፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ወግደረስን በሄኖክ መኮንን(18) የተካው የጌታቸው ዳዊቱ ደደቢት ከፊት በሁለት አጥቂ በ4-4-2 ቅርፅ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡  ይህ ቅያሪ ቡድኑ ከመጀመሪያው ግማሽ የተሻለ እንዲቀሳቀስ ረድቶታል፡፡ ነገር ግን በአጨዋወቱ የአጥቂ አማካይነት ሚና የኖረውን የሳምሶንን የተለመደውን ተፅዕኖ በበቂ ሁኔታ ለመመልከት የዘገየውን የክዌሲ ኬሊን የ71ኛ ደቂቃ ቅያሪ መጠበቅ የግድ ነበር፡፡ ኩዊሳን ቀይሮ የገባው ተስሎች ሳይመን(24) ከተከላካዮች ፊት በመሆን በተረጋጋ መንገድ ኳስን በማስጣል በሜዳው ስፋት ለተከላካዮች በቂ ሽፋን በመስጠት ሳምሶን ጥላሁን የቀረውን ደቂቃ በአመዛኙ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ ጊዜውን እንዲያሳልፍ አግዞታል፡፡ ይህ የሳምሶን ሚና ወደፊት መጠጋት ቡድኑ ወደ 4-1-3-2 አይነት ቅርፅ ኖሮት የማጥቃት ሀይሉንም አጠናክሮለት ታይቷል (ምስል 3) ፡፡
ከዚህ በኋላ ደደቢት ከፊት ባሉት ሁለት አጥቂዎቹ የተሻለ እድሎችን ለመፍጠር ችሎም ነበር፡፡  የማጥቃት ኃይሉንም ጨምሮ ብርሀኑ ቦጋለን ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት በመመለስ ተካልኝን ቀይሮ የገባው ጆሴፍ አባዮኬን(28) በጋራ መስመር አማካይነት ተጠቅሟል (ምስል3)፡፡  ባጠቃላይ ቡድኑ ጨዋታው እየገፋ በሄደ ቁጥር ወደትክክለኛው ቅርጽ እየመጣ ነበር ፡፡
ምናልባትም የ71ኛው ደቂቃ ቅያሪ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ደደቢት ከጨዋታው ጎል የማግኘት እድሉን ያሰፋለት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

image-5691f85b1d29a10dbb0d6e29575699f2029feeb3d0641e7c053f085479e96a2e-V

የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሳምንት ቀጥለው ሲካሄዱ ረቡዕ 9 ሰዓት ላይ ደደቢት መከላከያን ሲገጥም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ጨዋታ ቀጥሎ በ11፡30 አርባምንጭ ከነማን ከአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *