ኢትዮጵያዊው የመሃል ተከላካይ ዋሊድ አታ በኦስተርሰንድስን መለያ የመጀመሪያ ግቡን ትላንት ማምሻውን በተደረገ የስዊድን ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ኦስተርሰንድስ በሜዳው ያምክራፍት አሬና በኦርብሮ 4-2 ሲሸነፍ ዋሊድ ሁለት ግቦች ከመረብ አዋህዷል፡፡
ዋሊድ በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ኦስተርሰንድስ ከገፍሊ 0-0 በተለያየበት ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ የተሰለፈ ሲሆን ዕረቡ ምሽት በተደረገው ጨዋታ ኦስተርሰንድስ ቀዳሚ የሆነበትን ግብ በ39ኛው ደቂቃ አስመዝግቧል፡፡ ኦርብሮ በምሽቱ ኮከብ በነበሩት በካርል ሆልምበርግ እና ዳንኤል ጉስታቭሰን ተከታታይ ግቦች 4-1 መምራት ችሏል፡፡ ሆልምበርግ እና ጉስታቭሰን ሁለት ሁለት ግቦችን በስማቸው ሲያስመዘግቡ ዋሊድ ኦርብሮን 4-1 መሪነት ከማጥበብ የዘለለ ፋይዳ ያልነበራትን ግብ በ69ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡
በጥር የዝውውር መስኮት መከፈትን ተከትሎ ከቱርኩ ገልሰንበርሊጊ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት ያፈረሰው ተከላካዩ በኦስተርሰንድን መልካም እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል፡፡ በሊጉም ከተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ ሙሉ 90 መጫወት ችሏል፡፡
ሽንፈቱን ተከትሎ ኦስተርሰንድስ በደረጃ ሰንጠረዡ በስምንት ነጥብ 10ኛ ሲሆን ሊጉን የአምናው ሻምፒዮን ኖርኮፕኢንግ በ12 ነጥብ ይመራል፡፡ ኦርብሮ እና ዮንከፕኢንግስ ሶድራ ተከታዮቹን ደረጃዎች በ12 እና በ11 ነጥብ ሲይዙ ፋልከንበርግስ፣ ኤልፎስበርግ እና ቢኬ ሃከን ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የጨዋታውን ሃይላይት ለማየት ይህን ይጫኑ:- https://www.youtube.com/watch?v=Sg1l6jUU7JU