በአልጄሪያ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና በሳይፕረስ ሊጎች ተጫውቶ ዘንድሮ ለኢትዮዽያ ቡና በመፈረም ጥሩ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ካሜሩናዊው ያቡን ዊልያም ከሶከር ኢትዮዽያ ያደረገውን ቆይታ እነሆ እንዲህ ባለ መልኩ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ህይወት በኢትዮጵያ እንዴት ነው?
እጅግ በጣም ጥሩ ነው ፣ የቡድኑ አባላት እንደ ቤተሰብ ነው የምንኖረው፡፡ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ቋንቋ አላስቸገረህም ለመግባባት?
አይ በፍፁም አላስቸገረኝም፡፡ ከቡድኑም ጋር በደንብ ተግባብተን እየሰራን ነው፡፡ ህዝቡ በጣም አሪፍ ነው ፡፡ ግልፅነታችሁ. . . ኦ በጣም የሚገርም ነው፡፡ እኔ ደቡብ አፍሪካን ፣ አልጄሪያን አይቻለው፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ታማኝ እና ግልፅ ህዝብ አላየሁም፡፡ በጣም የተለየ ህዝብ መሆኑ ነገሮችን አቅልሎልኛል፡፡
ምግብስ እየተስማማህ ነው?
ኦ በጣም፡፡ እንጀራ በጣም ተስማምቶኛል፡፡ ቀን በቀን ባይሆንም በደንብ ነው የምመገበው፡፡ በጣም ተመችቶኛል ወድጄዋለው፡፡
በመጀመርያ ወደ ኢትዮዽያ የመጣኸው በቅዱስ ጊዮርጊስ አማካኝነት ነበር፡፡ እንዴት ለቡና ልትፈርም ቻልክ?
አዎን እውነት ነው ወደ ጊዮርጊስ ያመጣኝ የቡድኑ አሰልጣኝ ነው፡፡ አሁን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያይቷል፡፡ እኔና አንድ ካሜሩናዊ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሙከራ ጊዜ ለመሳለፍ ነበር የመጣነው፡፡ እዚህ በመጣሁ በሁለተኛው ቀን ሰዎች ከአቶ ገዛኸኝ ጋር አስተዋወቁኝ፡፡ እንደተዋወቅን ኢትዮዽያ ሆቴል ተቀጣጥረን ሲቪዬንና ቪዲዮዎችን ይዤለት ሄድኩ፡፡ ፊልሞቹንና ሲቭዬን ካየ በኋላ ሜዳ ላይ ሊመለከቱኝ እንደሚፈልጉ ነገረኝ፡፡ ራሴን ለማሳየት አንድ ዕድል በቂዬ እንደሆነ ለራሴ ነግሬዋለሁ፡፡ በቀጣዩ ቀን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴዬ ደስተኛ የሆኑት 15 ደቂቃ ብቻ አይተውኝ ነበር፡፡
አሁን በቡና ደስተኛ ነህ ?
በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር ከጠበቅኩት በላይ ነው፡፡ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
በተከታታይ ግቦች እያስቆጠርክ ነው…
በተከታታይ ጎል እያገባው ነው፡፡ በርግጥ ጎል ማግባት ስራዬ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ግቦች ለቡድናችን በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ዙር ውጤታችን ጥሩ አልነበረም ፤ አሁን ግን እጅግ በጣም ተሻሽለናል ፤ በደረጃ ሰንጠረዡም ወደፊት መጥተናል፡፡ በተከታታይ እያሸነፍን ነው፡፡ በራስ መተማመናችን በጣም ጨምሯል፡፡ ይህ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡
በግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ ላይ በአንድ ጎል አንሰህ ሁለተኛ ነህ፡፡ ምን ይሰማሃል?
የተቀጠርኩት ጎል ላስቆጥር ነው፡፡ በሰንጠረዡ 2ኛ በመሆኔ ምንም የተለየ ስሜት አይሰማኝም፡፡ እኔም ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ዋናው ነገር የቡድናችን ጥሩ መሆን ነው፡ እኔ ቅድሚያ የምሰጠው ለኢትዮዽያ ቡና ውጤት ነው፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነት ሩጫው ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ዋናው የብድን ውጤት ማማር ነው፡፡ ጓደኞቼ ጥሩ ኳስ ባያቀብሉኝ እኔ ጎል ማግባት አልችልም፡፡
አሁን በቡና እየተጫወትክበት ያለውን ቦታ ትወደዋለህ ? ኳስ ስትቀበል ከተጋጣሚ የግብ ክልል ርቀህ መሆኑና እንቅስቃሴህ በመስመሮች እና በመሃል ሜዳ ላይ መሆኑ የአጨዋወት ባህርይህ ነው ወይስ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው?
ብዙ ጊዜ አሰልጣኝ ፖፓዲች ወደኋላ በጥልቀት ተመልሼ እንድጫወት ፣ በቡድኑ እንቅስቃሴ ላይ እንድሳተፍ ፣ በመከላከሉም እንድሳተፍ ይነግረኛል፡፡ እኔም ይህን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔ ከዘጠኝ ተጨዋቾች ፊት የመጨረሻ አጥቂ ሆኜ ብጫወት የበለጠ እመርጣለው፡፡ ቢሆንም ግን አሰልጣኙ የራሱ የሆነ አመለካከት አለው፡፡ እኔ ወደ ኋላ ተመልሼ በመጫወቴም አይከፋኝም ፤ ብዙ ጎልም እያስቆጠርኩ ነው፡፡
እጅግ በጣም አስፈላጊ ግቦችን እያስቆጠርክ ነው፡፡ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በአንተ ግቦች ብቻ በተመሳሳይ ውጤት አሸንፋችኀል፡፡ ጎሎችህ ለክለቡ አስፈላጊ በመሆናቸው የተነሳ በቡድኑ ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ሰው ነኝ ብለህ ታስባለህ ?
(ሳቅ) ኧረ በፍፁም አላስብም፡፡ ይሄ የእግርኳስ ባህሪ አይደለም፡፡ እግር ኳስ የቡድን ጨዋታ ነው ፤ ለምሳሌ የመሀል ሜዳ ተጨዋቾች ጥሩ ኳስ ባያቀብሉኝ እኔ ማግባት አልችልም፡፡ አሁን ደግሞ ከዕለት ዕለት እየተሻሻልን ነው፡፡ የተከላካይ ክፍላችን ምንም ጎል አልተቆጠረበትም፡፡ የመሃል ሜዳ ተጨዋቾቻችን በየጨዋታው በመሀል ሜዳ ተጋጣሚን ይበልጣሉ፡፡ አንደ ቡድን በጣም ተሻሽለናል፡፡ ጎል የነዚህ ሁሉ ውጤት ነው ፤ የኔ ብቻ አይደለም፡፡
የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎችን እንዴት አገኘሃቸው?
ኦ! ደጋፊው የሚገርም ነው፡፡ በጣም ነው የምወዳቸው፡፡ የግድ እንድትጫወት ያደርጉሃል፡፡ በጣም ነው የሚያግዙህ፡፡ ሌሎቹን ክለቦች እያቸው፡፡ (ደጋፊ የሌላቸውን ማለቴ ነው) ሜዳ ልትጫወት ስትገባ ምንም የተለየ ስሜት እና የማሸነፍ ተነሳሽነት አይኖርህም፡፡ የቡና ደጋፊዎች ግን ከሜዳ ውጭ ሳይቀር ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ በአዳማ ከባለ ሜዳዎቹ በላይ የቡና ደጋፊዎች ይበዙ ነበር፡፡ ሜዳ ላይ ሲዘምሩ ስናያቸው አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን አምነን እንጫወታለን፡፡፡ የኛ ደጋፊዎች የሚገርሙ ናቸው ያነቃቃሉ ያነሳሳሉ፡፡
በክለብ ውስጥ ከተጫዋቾች ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ቅድም እንዳልኩህ ቤተሰብ ሆነናል፡፡ በጣም እንግባባለን ፣ እርስ በእርስ እንገባበዛለን ፤ ምንም ችግር የለብንም፡፡ በነገራችን ላይ ከሜዳ ውጪ ጥሩ ባንሆን ውጤቱን ሜዳ ላይ ታየው ነበር፡፡ ከሜዳ ውጭ በጣም ጥሩ ስለሆንን ነው ውጤታችን ጥሩ የሆነው፡፡ ስናሸንፍም ስንሸነፍም እኩል እንመካከራለን ፤ በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡
በጣም የምትቀርበው ጓደኛህ ማነው?
አብዱልከሪም መሐመድ እና ፓትሪክ ቤናውን ናቸው፡፡ ከሪም ይመቸኛል ፤ አብረን ስንሆን ደስ ይለኛል፡፡ በቃ ከሪም የተለየ ሰው ነው፡፡
ፓትሪክ የረዥም ጊዜ ጓደኛዬ ነው፡፡ በአልጄርያ አብረን ነበርን ፤ አሁን ደግሞ እዚህ ተገናኘን፡፡ በደንብ እንተዋወቃለን እንግባባለን፡፡
ካንተ በተቃራኒ ከተሰለፉት ተከላካዮች አስቸጋሪ የምትለው ማን ነው?
ስሙን አላቀውም፡፡ (ቶማስ ስምረቱ ማለቱ ነው) የሚጫወተው ግን ለወላይታ ድቻ ነው፡፡ አይኔ አካባቢ በክርን መትቶኝ ቀዶኛል፡፡ (የተጎዳው የፊቱን ክፍል እያሳየ) በጣም ሃይል ቀላቅሎ የሚጫወት ተከላካይ ነው፡፡ የደደቢቱ አይናለምም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
ላንተ ምርጡ ኢትዮዽያዊ ተጨዋች ማነው?
(ሳቅ) ያው እኔ ከራሳችን ጨዋታዎች ውጪ ብዙ አላየሁም፡፡ ነገር ግን የሃዋሳ ከተማ የመስመር ተጫዋች ስሙን አላቀውም (አስቻለው ግርማ ማለቱ ነው) በጣም እወደዋለው፡፡ ብሔራዊ ቡድንም ይጫወታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እንደተጫወተ ሰምቻለሁ፡፡ ከሃገሩ ወጥቶ መጫወት የሚያስችል ብቃት አለው፡፡