ቡናማዎቹን ከብርቱካናማዎቹ የሚፋለሙበት ተጠባቂ ጨዋታ ረፋድ ላይ ይከናወናል።
በሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም እና በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ባለው ፉክክር ለመዝለቅ ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ።
ቡናማዎቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ከመሪው አርቋቸዋል። ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎች ነጥብ ተጋርቶ ተከታታይ ድሎች ካስመዘገበባቸው ሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በተከናወኑ ሦስት መርሐ-ግብሮች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሦስቱን ብቻ ማሳካቱም ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ወደ አስራ ሁለት ነጥብ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
ሽንፈት ባስተናገደበት መርሐ-ግብር
በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ ያልነበረው ቡድኑ በጨዋታው በጊዜ ግብ ማስተናገዱ ጎዳው እንጂ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ነበር። ኳሱን በተሻለ በመቆጣጠር ከወገብ በታች በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ የነበሩትን የሲዳማ ተጫዋቾች ለማስከፈት ቢታትርም በወረዱ የውሳኔ አሰጣጥ እና የስልነት ችግር አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም። ቡናማዎቹ ተከታታይ ድሎች ባስመዝገቡባቸው ጨዋታዎችም ጭምር የግብ ማስቆጠር ችግር ተስተውሎባቸዋል፤ በ24ኛው ሳምንት በባህርዳር ከተማ ከገጣማቸው ሽንፈት በፊት በተከናወኑ ስድስት መርሐ-ግብሮች ላይ አራት ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ በጨዋታዎቹ እንደሚፈጥራቸው ዕድሎች ግብ ሳያስቆጥር ቢዘልቅም አንድ ግብ ባስቆጠረባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ግን የአፈፃፀም ድክመቱ በጉልህ ታይቷል። ይህንን ተከትሎ በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች በተጋጣሚ የግብ ክልል ያለው ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም ለስድስት ተከታታይ መርሐ-ግብሮች ምንም ግብ ሳያስተናግድ በጥንካሬው ከዘለቀ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ወደ ቀድሞ ጥንካሬው መመለስም አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሚጠብቃቸው ሌላው የቤት ስራ ነው።
ሀያ ዘጠኝ ነጥቦች በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከተደቀነናቸው የስጋት ቀጠና ለመራቅ ድልን እያለሙ ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።
ድሬዳዋ ከተማዎች በዝናብ፣ በመብራት መቆራረጥ እና በብዙ ክስተቶች ታጅቦ በተጠናቀቀው የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ሽንፈት ብያስተናግዱም ከቀደመው አካሄዳቸው በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ሆኖም በታችኛው ፉክክር ውስጥ ከሚገኙት ቡድኖች በላቀ መንገድ ለመፎካከር ለውጡን በተቻለ ፍጥነት በውጤት ማጀብ ከምንም በላይ አስፈላጊው ነው።
ከዚህ አንፃር ካሳለፋቸው አራት ግብ አልባ የጨዋታ ሳምንታት በተለየ ባለፉት አራት መርሐ-ግብሮች ተሻሽሎ አምስት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመሩ ጥንካሬ መቀጠል የሚገባው አወንታዊ ጎን ነው።
በቅርብ ጨዋታዎች መጠነኛ መንገራገጮች ቢገጥሙትም የኢትዮጵያ ቡና የኋላ ክፍል በቀላሉ ግቡን የሚያጋልጥ ስላልሆነ የሚገኙ አጋጣሚዎችን በስልነት መጠቀምም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ብርቱካናማዎቹ በሜዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር ከፍ እንደሚል በሚገመትበት ጨዋታ የሚስያመዘግቡት ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው፤ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት መውጫ በሩ ላይ የቆመው ሀዋሳ ከተማ በቅርብ ሳምንታት ያስመዘገበው ውጤትም የነገው ጨዋታ ለድሬዳዋ ከተማ ያለው ትርጉም ከፍ ያደርገዋል።
ድሬዳዋ ከተማዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው መሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ዋና አሰልጣኙ ይታገሱ እንዳለ ግን በተጣለባቸው ቅጣት ምክንያት ቡድናቸውን አይመሩም። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ ከጉዳቱ አገግሞ ትናንት ቡድኑን የተቀላቀለ ሲሆን ለነገው ጨዋታ ግን አይደርስም፤ ከዚህ ውጭ ሌሎች የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 25 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 14 በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ይዟል። 6 ጨዋታ አቻ የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ 5 ጨዋታ አሸንፏል። ቡናማዎቹ 42፣ ብርቱካናማዎቹ 24 ጎሎች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)