በዛሬው ዕለት ከአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር በስምምነት የተለያዩት መቐለ 70 እንደርታዎች አዲስ አሰልጣኙ ለመሾም ተቃርበዋል።
ረፋድ ላይ ከአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር በስምምነት የተለያዩት መቐለ 70 እንደርታዎች አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም አዲስ አሰልጣኝ አድርገው ለመቅጠር ከጫፍ እንደደረሱ ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ታማኝ ምንጮች አረጋግጣለች።
በውድድር ዓመቱ ሀያ ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ርቀት የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ክለቡን የሚመራ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ለመቅጠር ከጫፍ ደርሷል፤ ከሳምንታት በፊት ከወልዋሎ ጋር በስምምነት የተለያየው አሰልጣኙ ዛሬ ከክለቡ የበላይ አመራሮች ጋር የተወያየ ሲሆን በቅርብ ሰዓታትም ሂደቱ ይቋጫል ተብሎ ይጠበቃል።
በእርሻ ሠብል ያሳለፋቸውን አይረሴ አስራ ሦስት ዓመታትን ጨምሮ ለአስራ ስድስት ዓመታት በተጫዋችነት ካሳለፈ በኋላ በ1990 ‘ታክሲ’ በተባለ ቡድን የአሰልጣኝነት ሂወቱን የጀመረው ፀጋዬ ለሦስት ዓመታት በታክሲ ቡድን ከሰራ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚገኙ ክለቦች የመሥራት ጉዞውን በ1993 የአብሮ አደጉ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ምክትል በመሆን በትራንስ ኢትዮጵያ ማሰልጠን የጀመረ ሲሆን ከ1997 ጀምሮ በዋና አሰልጣኝነት በትራንስ ኢትዮጵያ ፣ ሐረር ቢራ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ወልዋሎ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባጅፋር እና ወላይታ ድቻ ዘንድሮ ደግሞ ወልዋሎን አሰልጥኗል።
አሁን ደግሞ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ያለውን መቐለ 70 እንደርታ ለማሰልጣን ከጫፍ ደርሷል።