የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው 1ኛው ዙር ተጠናቋል፡፡ ጅማ አባ ቡና ካለሽንፈት 1ኛውን ዙር ሲያጠናቅቅ ሙገር ወደ ደብረብርሃን ተጉዞ አሸንፏል፡፡
ጅማ አባ ቡና አአ ዩኒቨርሲቲን አስተናግዶ 4-0 አሸንፏል፡፡ የምድብ ለ መሪዎቹን ግቦች አሜ መሃመድ እና ኪዳኔ አሰፋ ሁለት ሁለት ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የተመረጠው ኪዳኔ በጥሪው ማግስት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ጅማ አባ ቡና በ1ኛው ዙር ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 12 በማሸነፍ በሶስት ጨዋታ አቻ በመውጣት ምንም ሽንፈት ሳይቀምስ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡
ወደ ደብረብርሃን የተጓዘው ሙገር ሲሚንቶ ሰሜንሸዋ ደብረብርሃንን 1-0 አሸንፏል፡፡ የሙገርን ብቸኛ የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ኤሪክ ኤልማን ነው፡፡
የሁለተኛው ዙር ግንቦት 9 የሚጀመር ሲሆን የ1ኛው ዙር ግምገማ ግንቦት 3 ይደረጋል፡፡