ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| መቐለ 70 እንደርታ ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| መቐለ 70 እንደርታ ከ ሲዳማ ቡና

መቐለ 70 እንደርታ የመትረፍ ዕድሉን ለማለምለም ሲዳማ ቡና ደግሞ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ይጀመራል

በሰላሣ አራት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበትን ዕድል ለማመቻቸው ድልን እያለሙ ወደ ሜዴ ይገባሉ።

ስሑል ሽረን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ምዓም አናብስት ከተጋጣሚያቸው በላይ ነጥቦቹ እጅግ የሚያስፈልጉት ጊዜ ላይ ይገኛል፤ በነገው ዕለት ድል ማድረግ የሚችል ከሆነ አንድ ደረጃ መሻሻል ከማግኘቱም በላይ ብያንስ እስከ ዕለተ ሐሙስ ከኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ዕድል የሚሰጠው እንደመሆኑም መርሐ-ግብሩ እጅግ ወሳኝ ነው። ምዓም አናብስት ምንም እንኳን ሙሉ ነጥብ ማሳካት ባይችሉም ዐፄዎቹን በገጠሙበት ጨዋታ የተሻለ ብልጫ ወስደው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል፤ ሆኖም በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ካልቻሉ በየሳምንቱ ነጥብ ይዘው በመውጣት ላይ ከሚገኙት የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ወደ ኋላ ስለሚያስቀራቸው በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የታየባቸው ጉልህ የአፈፃፃም ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መምጣት በኋላ መጠነኛ መነቃቃት ያሳየው ቡድኑ ኳስን የሚቆጣጠርበት እንዲሁም ዕድሎች የሚፈጥርበት መንገድ ከጨዋታ ጨዋታ ማሻሻል ቢችልም የጨዋታ ውጤት ቀያሪ ዕድሎች ማባከን ግን ትልቁ ድክመቱ ነው። ይህንን ተከትሎ በጨዋታዎች የሚፈጥሯቸው ዕድሎች በቁጥርም ሆነ በጥራት ከፍ ማድረግ እና የአፈፃፀም ችግሩን መቅረፍ ከቡድኑ ይጠበቃል።

በአርባ ስድስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ከሚጠበቅባቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ይፋለማሉ።

አራት ነጥቦች ብቻ ከጣሉባቸው ስምንት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በመሪው መድን ሽንፈት አስተናግደው ወደ ጨዋታው የሚቀርቡት ሲዳማ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው አንፃር ሲታይ ቀለል ባለ ጫናና ውጤት ፈላጊነት የሚገቡ ቢሆንም በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ የአንድ ደረጃ መሻሻል ይሰጣቸዋል። በመድን ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመርያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ብልጫ የነበራቸው ሲዳማዎች በተጠቀሱት ደቂቃዎች ያገኟቸውን ዕድሎች ባለመጠቀማቸው እና በመከላከሉ ረገድ በሰሯቸው ስህተቶች ለሽንፈት ቢዳረጉም ያሳዩት እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። ይህንን ተከትሎ ከሽንፈቱ በፊት በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች በማስቆጠር በጥሩ ብቃት የነበረው እንዲሁም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን አስከብሮ ከወጣ በኋላ ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው በነገው ዕለት መሻሻል የሚገባቸው የቡድኑ ክፍሎች ናቸው።

በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ኪሩቤል ኃይሉ ከቅጣት ተመልሷል፤ ጉዳት ላይ የሰነበተው ጋናዊው ተከላካይ ቤንጃሚን ኮቴ ግን አገግሞ ባለፉት ቀናት ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል ጊት ጋትኩት ከቅጣት ሲመለስ መስፍን ታፈሰ ግን በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አጥቂው ማይክል ኪፕሩቪ ከጉዳት ቢያገግምም በሙሉ ጤንነት ለወሳኙ የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ለማድረስ ከነገው ጨዋታ ውጭ ከመሆኑ በቀር የተቀሩት የቡድኑ ስብስብ ተሟልተው የሚቀርቡ ይሆናል።

ቡድኖቹ እስካሁን ባደረጓቸው 5 ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ድል አድርገው በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ከተቆጠሩት 11 ጎሎች መቐለ ስድስቱ ሲያስቆጥር ሲዳማ አምስቱን አስቆጥሯል።