ሸገር ደርቢ፡ ከጨዋታው በኋላ የተሰጡ አስተያየቶች

የሸገር ደርቢ ጨዋታቸውን ካለግብ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ማርቲነስ ኤግናተስ ኖይ እና የኢትዮጵያ ቡናው ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

“ደጋፊው ጥሩ ጨዋታ ተመልክቷል ብዬ አስባለው” ማርት ኖይ

ስለጨዋታው

ደጋፊው ጥሩ ጨዋታ ተመልክቷል ብዬ አስባለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንደዚህ ዓይነት ጥሩ እግርኳስ በተጫወትን ቁጥር እግርኳሱ ያድጋል፡፡ ቡና ከጊዮርጊስ በጣም ከባድ ጨዋታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚካሄዱት ግጥሚያዎች የተለየው ጨዋታ ነው፡፡ ስለዚህም ሁሌም የተለየ እና ያልተጠበቀ ነገር ያጋጥማል፡፡ ሜዳ ላይ እና በስታዲየም ውስጥ የተፈጠረ ችግር አልነበርም፡፡ ተስፋ አለኝ ከስታዲየም ውጪም ምንም ችግር እንደማይፈጠር፡፡ ሁለቱም ክለቦች በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ስለነበሩ ጥቂት የግብ ሙከራዎችን ብቻ ልናይ ችለናል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬው እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”

ስለአስቻለው የቀኘ መስመር ተከላካይነት ሚና እና ጎዲዊን ቺካ

” አስቻለው ያለቦታው ነው የተሰለፈው፡፡ በቀኝ ተከላካይ መስመር የተጫዋች ዕጥረት ስለነበረብን ነው (አሉላ ግርማ ጉዳት ላይ ነው)፡፡ ጎድዊንን በሁለት ጨዋታ ጥሩ አይደለም ብሎ መደምደሙ አግባብ አይደለም፡፡ ”

image

“በውጤቱ ደስተኛ አይደለሁም” ድራጋን ፖፓዲች

ስለጨዋታው
” ያለግብ አንድ ክለብ ማሸነፍ አይችልም፡፡ ጥሩ ግብ የማግባት ዕድሎች አግኝተን አልተጠቀምንባቸውም፡፡ ዛሬ ያለ ሁለት አጥቂዎቻችን (ዊሊያም እና ሳሪል) ነው ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ ይህም ያለግብ አግቢ ወደ ሜዳ እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ይህ ትልቁ ችግራችን ነበር፡፡ እኔ እንደማስበው ከሆነ ቡድኔ ጥሩ ተጫውቷል፡፡ እነአማኑኤል፣ አህመድ እና ጠቅላላ ቡድኑ የተቻላቸውን ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ የቀረን ነገር ቢኖር ጥሩ ግብ አስቆጣሪ ብቻ ነበር፡፡ ደጋፊዎቻችን በውጤቱ እንደማይደስቱ እና እንደማይከፉ አውቃለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓምና ሻምፒዮን በመሆኑ ለነሱ ክብር አለን፡፡ በሚቀጥለው የደደቢት ጨዋታ ጥሩ ለመሆን እንጥራለን፡፡ በውጤቱ ደስተኛ ልሆን አልችልም ነገር ግን አልተከፋሁም፡፡”

ስለመስኡድ አለመሰለፍ

“ካሉን ተጫዋቾች መካከል አንዳንዶቹ ድካም ላይ ናቸው፡፡ ባለፈው ጨዋታ እኔ ሆስፒታል ነበርኩ መስኡድ በድካም ምክንያት ተቀይሮ እንደወጣ ሰምቻለው፡፡ በሚቀጥሉት ጨዋታዎች የምንጠቀመው ይሆናል፡፡ መስኡድ ጥሩ ተጫዋች፣ አምበል እና መሪ ነው፡፡ ወደ ቡና ከመጣው ጀምሮ ከመስኡድ ጋር ችግር የለብኝም፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *