የ33ኛው ሳምንት በሁለት ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖች ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ በሚፋለሙበት ጨዋታ ይጠናቀቃል።
12 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ለተጋጣሚዎቹ ብቻ ሳይሆን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያሉ እና ለቀጠናው የቀረቡ ቡድኖችን ሁሉ ይመለከታል። ሁለቱ ቡድኖች ነገ የሚያሳኩት ነጥብ አጠቃላይ የቀጠናውን እንድምታ የሚወስን ቢሆንም በይበልጥ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋን ለመስነቅ ወሳኝ ይሆናል።
ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተጋረጠበት የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ከድል ጋር ከተራራቀ ሰባት ጨዋታዎች ያለፉት እና ተመሳሳይ ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ እያለመ ወደ ሜዳ የሚገባውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገጥማል። ኤሌክትሪኮች ባሳለፍናው ሳምንት ድላቸው መጠነኛ እፎይታ ማግኘት ቢችሉም ተከታዮቻቸው መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማ ድል አድርገው የነጥብ ልዩነቱን ማጥበባቸው ተከትሎ ዳግም ውጥረት ውስጥ ገብተዋል። የሁለት ደረጃዎች መሻሻል ለማግኘት እንዲሁም ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ የነገውን ውጤት አጥብቆ የሚፈልገው ቡድኑ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ወሳኝ ድል አሳክቶ ወደ ነገው ወሳኝ ፍልሚያ መቅረቡ በአእምሮ ረገድ ተጠቃሚ የሚያደርገው ጉዳይ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት ሙከራዎች በተደረገበት የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የማጥቃት ጥንካሬ ግን በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ነው። በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለውን አቀራረብ ላይ ለውጦች ማድረግም አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚጠብቃቸው የቤት ስራ ነው።
ድል ካደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት እና በሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገቧቸው ውጤቶች ለስጋት ቀጠናው ቀርበዋል። የአምናው ሻምፒዮኖቹ በወራጅ ቀጠናው ካለው መቐለ 70 እንደርታ በሦስት ነጥብ ርቀት ብቻ መገኘታቸውም ወደ ነገው ጨዋታ ድልና ድልን ብቻ እያለሙ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከድል ጋር በተራራቁባቸው ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ውስጥ አራት የአቻ እና ሦስት ሽንፈቶች ከማስመዝገባቸውም በላይ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ተከታታይ ድሎች ማሳካታቸው እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች የገጠማቸው ሽንፈቶች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እና ለመራቅ እያለሙ ወደ ሜዳ በገቡት አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መሆኑ ቡድኑ ለስጋት ቀጠናው ይበልጥ እንዲቀርብ አድርጎታል። በነገው ዕለት ከናፈቃቸው ድል ጋር ከታረቁ በሰንጠረዡ የአንድ ደረጃ መሻሻል የሚያገኙት ሀምራዊ ለባሾቹ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በበርከት ያሉ ጉዳዮች መሻሻል ይኖርባቸዋል። ቡድኑ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት መርሐግብር ላይ በአመዛኙ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችልም ጉልህ መከላከል ጉድለቶች እንዲሁም ነገሮች በጥድፊያ የመከወን ችግር ተስተውሎበታል። ይህንን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ማሻሻል እንዲሁም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚስተዋለው ጥድፍያ ማረም የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የቤት ስራዎች ናቸው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽመክት ጉግሳን በቅጣት አብዱላሂ አላዮን ደግሞ በጉዳት በነገው ጨዋታ የሚያጣ ይሆናል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ኪቲካ ጅማ በቅጣት፤ ባሲሩ ኡማር እና ናትናኤል ዳንኤል ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ከመሆናቸው ውጭ የተሟላ ስብስቡን ይዞ ይቀርባል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚ ቀደም በሊጉ 35 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። ኤሌክትሪክ 13 አሸንፎ 51 ጎሎች ስያስቆጥር፤ ባንክ 11 አሸንፎ 43 ጎሎች አስቆጥሯል። በ 11 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።