ዘላለም አባተ በዘንድሮው ውድድር ምርጡን ጎል ባስቆጠረበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ ዐፄዎቹን 3ለ0 ሲያሸንፉ ዐፄዎቹ በወራጅ ቀጠናው ባለው ውጥረት ውስጥ ቀጥለዋል።
ፋሲሎች 1ለ1 ካጠናቀቁት የመቐለው ጨዋታ በአራቱ ቋሚዎች ላይ ቅያሪን ሲያደርጉ እዮብ ማቲያስን በዳንኤል ፍፁም ፣ አቤል እያዩን በአቤል እንዳለ ፣ ቢኒያም ላንቃሞን በቢኒያም ጌታቸው ፣ አንዋር ሙራድን በቃልኪዳን ዘላለም ከኤሌክትሪክ ጋር በተመሳሳይ 1ለ1 አጠናቀው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በአምስቱ ለውጥ ሲያደርጉ አብነት ይስሀቅ ፣ ኬኔዲ ከበደ ፣ ፍፁም ግርማ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሠ እና ሙሉቀን አዲሱን በቢኒያም ገነቱ ፣ ናትናኤል ናሲሩ ፣ አብነት ደምሴ ፣ ብዙአየው ሰይፈ እና ተስፋዬ መላኩ በመተካት ገብተዋል።
ፋሲሎች ካንዣበበባቸው የወራጅ ስጋት ለመላቀቅ ድቻዎች በበኩላቸው ነጥባቸውን በማሳደግ በሊጉ ለመቆየት የሚወስንላቸውን ውጤት ለመያዝ ምሽቱን የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ውጤቱን እንደሚፈልግ ቡድን ከፍ ያለ አልነበረም። ፋሲሎች ፈጥነው ቢኒያም ጌታቸው ሳጥን ውስጥ ያለቀለት አጋጣሚን ካመከነ በኋላ በአመዛኙ ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪዎቹ ሀያ ደቂቃዎች በይበልጥ በመልሶ ማጥቃት በመጫወት የአፄዎቹን የመከላከል ስህተት መጠቀም የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የጀመሩት ከ16ኛው ደቂቃ ጀምሮ ነበር። መሳይ ኒኮል ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ መሳይ ሠለሞን የግብ ዘቡን ዮሐንስ ደርሶን ከግብ ክልል መውጣት ተመልክቶ ቢመታም በግቡ የግራ ቋሚ ብረት ታካ ኳሷ ከወጣችበት በኋላ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን እየወሰዱ ቢመጡም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ፍፁም መረጋጋት የማይታይባቸው ፋሲሎች በ49ኛው ደቂቃ በሰሩት የመከላከል ስህተት ጎል ተቆጥሮባቸዋል።
መሐል ሜዳው ላይ መሳይ ኒኮል በቢኒያም ጌታቸው ላይ ጥፋት በመስራቱ የፋሲሉ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተቃውሞ ሲያሰሙበት የነበረችዋን ኳስ የዕለቱ ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በማስቀጠላቸው ውብሸት ወደ ቀኝ ሰጥቶ ፀጋዬ ብርሀኑ ወደ ውስጥ ሲያሻግር መሳይ ሠለሞን ከመረብ አሳርፎ የጦና ንቦቹን መሪ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር ከሁለት ደቂቃ መልስ በጥሩ የእግር ስራ የድቻ ሦስተኛው ሜዳ ላይ የደረሱት ፋሲሎች ከቀኝ ሳጥን ቢኒያም ጌታቸው በአንድ ለአንድ ግንኙነት ከቢኒያም ገነቱ ጋር ተገናኝቶ ሞክሮ የግብ ዘቡ ቢኒያም በጥሩ ቅልጥፍና አድኖበታል። ወላይታ ድቻዎች አጋማሹ ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው መሳይ ሠለሞን ሌላ አጋጣሚን ቢያገኝም ሞኞት ደበበ ከኋላ ደርሶ ኳሷን አስጥሎታል።
ድቻዎች ጉዳት ባስተናገደው ዮናታን ኤልያስ ምትክ ያሬድ ዳርዛን ቀይረው በተመለሱበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሻሻለውን ፋሲል ከነማን ማስተዋል የቻልን ቢመስልም የቡድኑ የሦስተኛ ሜዳ አጠቃቀም ግን ፍፁም የተዳከመ ነበር። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ፍሰሀ እና ቢኒያም ጌታቸውን በአንዋር ሙራድ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በመተካት በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ወስደው በይበልጥ ወደ ሳጥኑ የሚያስጠጋቸውን እንቅስቃሴ ቢያዘወትሩም ጥራት ባላቸው ዕድሎች ግን ጥረታቸው የፈካ አልነበረም። ለኋላ ክፍላቸው ሽፋን በመስጠት የተጋጣሚያቸውን ማጥቃት ማቋረጥ ዋነኛ ስራቸው ያደረጉት የጦና ንቦቹ ጥቅጥቅ ባለው መከላከል ያስቆጠሯትን ግብ ማስጠበቅ ላይ ተጠምደው ቢታዩም ተጋጣሚያቸው ጥለው የሚሄዱትን ቦታ ለመጠቀም ሲዳዱ ተስተውሏል።
ጌታነህ ከበደ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት መቶ በአግዳሚው በላይኛው በኩል ከወጣችዋ ሙከራ በኋላ ለረጅም ደቂቃዎች ከእንቅስቃሴ በቀር ሙከራዎችን ባስናፈቀን ጨዋታ 87ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ከረጅም ደቂቃ መከላከል በኋላ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፋሲል ሳጥን የተገኙት ድቻዎች ያሬድ ዳርዛ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ተቀይሮ የገባው ዘላለም አባተ ኳሷን ዮሐንስ ደርሶ መረብ ላይ አሳርፏታል።
እንደነበራቸው የእንቅስቃሴ ጥሩነት የተቃራኒ ሜዳ ላይ መረጋጋት ያቃታቸው ፋሲሎች በጭማሪ ደቂቃ በድቻዎቹ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ተሰንዝሮባቸዋል። መሳይ ሠለሞን እና ዘላለም አባተ አከታትለው ሁለት ሙከራዎችን አድርገው ዮሐንስ እና ምኞት ደበበ ካመከኗቸው በኋላ በ97ኛው ደቂቃ እጅግ አስደናቂ ጎል ከመሐል ሜዳው ወደ ራሳቸው ሜዳ ካደላ ቦታ ላይ ዘላለም አባተ የዮሐንስ ደርሶን ከግብ ክልል መውጣት ተመልክቶ ከርቀት ያስቆጠራት ግሩም ጎል ወላይታ ድቻን በመጨረሻም 3ለ0 እንዲያሸንፍ አድርጎታል። ድሉም ወላይታ ድቻዎች በሊጉ መቆየታቸውን ሲያረጋግጡበት ፋሲሎች በበኩላቸው በሊጉ የወራጅ ስጋታቸውን ከፍ ያደረገ ውጤት ተመዝግቦበታል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በእንቅስቃሴ የተሻሉ መሆናቸውን ገልፀው የመጀመሪያዋ ጎል ስትቆጠር ቢኒያም ላይ ጥፋት ተሰርቶ ዳኛው ባለማስቆሙ በሽግግር እንደተቆጠረባቸው በዚህም የተነሳ የገባች ግብ ቡድኑን እንደረበሸባቸው በመጠቆም በዚህ ተራ ውሳኔ ደስተኛ አይደለሁም ካሉ በኋላ በጨዋታው የተጋጣሚያቸውን ማጥቃት እንደ ቡድን ባለመቆጣጠራቸው መሸነፋቸውን እና በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ በሊጉ ለመቆየት የራሳቸውን ዕድል በራስ መወሰን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የወላይታ ድቻው አቻቸው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በአንፃሩ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በእንቅስቃሴ የተሻልን ነን ያሉትን ሀሳብ አልቀበለም በማለት ከጀመሩ በኋላ ምን ጊዜም በእንቅስቃሴ የተሻለ ቡድን ጎል ያስቆጥራል የተሻሉም ስለሆኑ አስቆጥረው ማሸነፋቸው ትልቁ ነገር መሆኑን በደንብም ስለተጫወቱ እንዳሸነፉ እና ድሉም ለቀጣይ የኢትዮጵያ ዋንጫ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ጎል አስቆጣሪዎቹ መሳይ እና ዘላለምንም አድንቀዋል በተለይ ዘላለም ያስቆጠራት ሦስተኛዋ ጎል ድንቅ ነበረች ሲሉም ተደምጠዋል።