ሪፖርት| በአዲስ አበባ የተደረጉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ሪፖርት| በአዲስ አበባ የተደረጉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

ሁለት ቀይ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናና መቐለ 70 እንደርታ 1-1 ሲለያዩ አርባ ምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

ሀድያ ሆሳዕና ከ መቐለ 70 እንደርታ

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር የታየበት ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር የሚደረጉ ሙከራዎች ግን እጅግ አነስተኛ ነበሩ። በ14ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ 70 እንደርታው አጥቂ ፕሪንስ ኦፊሪ ከሞከረውና ግብ ጠባቂው ካደነበት ኳስ ውጭም ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያስመለክትም አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ግን መቐለዎች ፈጣን ለውጥ አሳይተዋል። በ49ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ እና ብርሃኑ አዳሙ የተዋጣለት የአንድ ሁለት ቅብብል ካደረጉ በኋላ ያቀበሉትን ኳስ ኬኔዲ ገብረጻዲቅ ከሳጥን ጠርዝ ላይ አክሮ በመምታት ምዓም አናብስትን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሀድያ ሆሳናዎችም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። በኢዮብ አለማየሁ እና በብሩክ በየነ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም እስከ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ድረስ የፈለጉትን ግብ ማግኘት ተስኗቸው ቆይተዋል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎችም እጅግ አስገራሚ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነበር። ዳግም ወንድሙ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ሀድያ ሆሳዕናዎች በጎደሎ ተጫዋች ቀሪውን ክፍለ ጊዜ ቢቀጥሉም በ90+7ኛው ደቂቃ ጸጋአብ ግዛው ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከግቡ በኋላ ካፒቴኑ ሄኖክ አርፍጩ በቀይ ካርድ ሲሰናበት ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

አርባ ምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የመጀመሪያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በወሰዱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ብርቱ እንቅስቃሴ የታጀበ ነበር። በተለይም ቢኒያም ካሳሁን በግንባር በመግጨት እንዲሁም ናትናኤል ዳንኤል ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚነትን ሊያስገኙ የሚችሉ ሙከራዎችን አድርገው ነበር።

በአንጻሩ አዞዎቹ በአመዛኙ በመከላከል ላይ ተመስርተው ለመጫወት ቢሞክሩም ቴዎድሮስ በንቲ ከሳጥን ውጭ አክሮ በመምታት የንግድ ባንክን ግብ ጠባቂ የፈተነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። ሆኖም ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 45 ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር ቢታይበትም ሁለቱም ቡድኖች ኳስና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የጨዋታ ብልጫቸውን አስቀጥለው በመስመር ጥቃቶች ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም መስመር አጥቂው ሁዜይፋ ሻፊ ከመስመር እየተነሳ ያገኘቻቸውን ሁለት ንጹህ የግብ ዕድሎች መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። በአጠቃላይ ሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማጥቃት ብልጫና በአርባ ምንጭ ብርቱ መከላከል የቀጠለ ቢሆንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ያለ ምንም ግብ (0-0) በአቻ ውጤት ተጠናቋል።