ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ወልዋሎዎች ቡናማዎቹን 4ለ2 ሲያሸንፉ ነጌሌ አርሲ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

ነጌሌ አርሲ ከ ፋሲል ከተማ
የጨዋታ ሳምንት በሁለተኛ ቀን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ የተደረገው ቀዳሚው ጨዋታ ሰጎኖቹን ከዐፄዎቹ አግናኝቷል። ቡድኖቹ እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ባደረጉበት በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ብቻ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ተመልክተናል፤ 19ኛው ላይ ደቂቃ ዐፄዎቹ በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ ሳጥን ሲገቡ ኪሩቤል ዳኛ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ቦና ቦካ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ ኳሱ ተጨርፎ በረከት ግዛው አግኝቶ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ በቀላሉ ከተቆጣጠረባቸው ሙከራ ውጪ ሌላ አስቆጪ የሚባል እንዲሁም ግብ ጠባቂዎቹን መፈተን የቻሉበትን ዕድል ሳይፈጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ነጌሌዎች ቀዳሚ ለመሆን በፈጣን ሽግግር በመስመሮች እየገቡ የግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ሳጥን ውስጥ ሲደርሱ ግን የጠራ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃው ላይ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ ገብረመስቀል ዱባለ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሞይስ ፖዋቲ በቅልጥፍና ያዳናበት እንዲሁም በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ከቤ ብዙነህ አግኝቶ በግሩም ሁኔታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው እንዴትም የመለሰባቸው አጋጣሚ ነጌሌዎቹን ባለቀ ደቂቃ አሸናፊ ለማድረግ የቀረቡ ወርቃማ ሙከራ ነበር።

ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ የገቡት ዐፄዎቹ ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል። ዳግም አወቀ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ሳጥን ውስጥ ለነበረው በረከት ግዛው የቀነሰለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም አግዶባቸዋል። እንዲሁም በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በጫና ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ሲደርሱ የተስተዋሉት ዐፄዎቹ በተለይም በቆሙ ኳሶች ሳጥን ውስጥ እየደረሱ ቆይተው 83ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፤ ኪሩቤል ዳኜ ከግራ መስመር ከፍ ያለ ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ግብ ጠባቂው ጨርፎ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ተቀይሮ የገባውና ብቻውን ሳጥን ውስጥ የነበረው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ሳይጠበቅ ኳሱን ከፍ አድርጎ ከግቡ አናት አሳልፎታል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቡድኖቹ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ የእርስ በርስ ተከላካይ መስመር የፈተኑበት ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት 0ለ0 ተቋጭቷል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ጅማሮውን ያደረገው የቡናማዎቹና የቢጫ ለባሾቹ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ገና በማለዳው ግቦች ተቆጥረውበታል። የመጀመሪያ ደቂቃ ሳይጠናቀቀ በዳዊት ገብሩ አደገኛ ሙከራ ጅማሮውን ያደረጉት ወልዋሎዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል፤ ዳዊት ገብሩ በግራ መስመር ኳስ ይዞ ገብቶ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ኮንኮኒ ሀፊዝ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ ግብ አስተናግደው ከአራት ደቂቃ ቆይታ በኋላ አቻ ሆነዋል፤ ሳጥን ውስጥ በአንድ ለአንድ ቅብብል ገብተው አቡበከር አዳሙ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አድኖበት እራሱን ኳስ ዲቫይን ዋችኩዋ አግኝቶ ብቻውን ለነበረው ለአቡበከር አሻግሮለት አጥቂው በጠንካራ ምት ወደ መረብ ላይ አሳርፎታል። ከአቻነት ግብ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ቡናማዎች መሪነቱን የተረከቡበት ሁለተኛ ግብ አግኝተዋል። ዲቫይን ዋችኩዋ ከእራሳቸው ሜዳ ክፍል በረጅሙ የጣለውን ኳስ በረከት ብርሃኑ ሳጥን ውስጥ በግሩም መጀመሪያ ንክኪ ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂውን አልፎ መሪ አድርጓቸዋል።

መሪነቱን ያስረከቡት ቢጫ ለባሾቹ በአጋማሹ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ግብ ማነፍነፋቸውን ቀጥለው 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን የተሻማውን ኳስ ሀፊዝ ኮንኮኒ ከሳጥን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ አድርጎ ፏአድ ኢብራሂም ከመስመር ከመለሰባቸው በረጅም ደቂቃ በኋላ የአቻነት ግብ አግኝተዋል፤ በየነ ባንጃ እና ዳዊት ገብሩ ተቀባብለው ያሻገሩት ኳስ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ የነበረው ያሬድ ከበደ ጠንካራ ኳስ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ አቻ አድርጓቸዋል። አራት ግቦችን የተቆጠሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በፈጣን ሽግግሮች ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረቡ ሙከራዎችን አስመልክቶ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቡናማዎች ዲቫይን ዋችኩዋ ከመሃል ሜዳ ባደረገውና ግብ ጠባቂው እና የግብ ብረት ተጋግዘው ባወጡበው ሙከራ ሁለተኛ አጋማሽ ሲጀምሩ ከደቂቃዎች በኋላ ቢጫ ለባሾቹ ሳይጠበቅ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ስምዖን ማሩ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያሻገረውን ኳስ በየነ ባንጃ መረብ ላይ አሳርፎ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ቡናማዎቹ በጨዋታው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት በሙሉ ኃይላቸው እያጠቁ ሲቀጥሉ ወልዋሎዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው አልፈው አልፈውም ቢሆን በመልሶ ማጥቃት እየገቡ የጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ መሪነታቸውን ከፍ አድርገዋል። ግብ ጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም ከሳጥን ውጭ ሆኖ ኳሱን ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ በፈፀመው ስህተት መነሻነት የተገኘችውን ኳስ ኮንኮኒ ሀፍዝ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ መትቶ በማስቆጠር ጨዋታው 4ለ2 እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

