ከዚህ ቀደም የሊጉን የስያሜ መብት ይዞ የነበረው ቤትኪንግ ከሊጉ ጋር ከተለያየ ሁለት ዓመታት ቢቆጠሩም ሱፐር ስፖርት ጨዋታዎችን በቀጥታ እያስተላለፈ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የውጤት ማሳያው ስፍራ ላይ መቀመጡ ግርታን ፈጥሯል። ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን በተመለከተ ማብራሪያ ለመፈለግ ጥረት አድርጋለች።
የኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፌዴሬሽኑ ወጥቶ በክለቦች መመራት ከጀመረ አምስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን ውድድሩም የምስል እና የስያሜ መብቱን ሸጦ በአንፃራዊነት በጥሩ ሂደት እየተመራ ይገኛል። ዘንድሮን ጨምሮ ያለፉትን ዓመታት የምስል እና የስያሜ መብት ጠቅልሎ የገዛው መልቲ ቾይዝ ወይም ሱፐር ስፖርት የስያሜ መብቱን ለቤትኪንግ በራሱ መንገድ ሰጥቶ ለሦስት ዓመታት ሊጉ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚል ስያሜ እየተጠራ ሲከናወን የነበረ ሲሆን ከ2016 ጀምሮ ግን ተቋሙ ከኢትዮጵያ ገበያ ስለወጣ የስያሜ መብቱ እንደተቋረጠ ተገልፆ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም አክሲዮን ማኅበሩ ሌላ የስያሜ መብት ባለቤት ለማምጣት እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበረም በተለያዩ መንገዶች ሲሰሙ የነበሩ ተጨባጭ መረጃዎች ነበሩ።
ታዲያ ይህ በሆነበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በቀጥታ የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት ከ33ኛ ሳምንት ጀምሮ ጨዋታዎችን ለተመልካቾች እያደረሰ በሚገኝበት ወቅት በቴሌቪዥን መስኮቱ ላይ በሚታየው የውጤት ማሳያ ሰሌዳ (Score board) የቤትኪንግ ሎጎ እንዳለ ለማስተዋል ችለናል። ከሊጉ እንደወጣ ተገልፆ የነበረው ተቋሙ በምን አይነት መንገድ ከሊጉ ጋር ዳግም ተገናኝቶ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ግልፅ ባይሆንም በስህተት ይሁን በምክንያት የተቋሙ ሎጎ መቀመጡ ግርታን ፈጥሯል።
የዝግጅት ክፍላችን ወደኋላ መለስ ብላ ባደረገችው ማጣራት ዓምናም ተመሳሳይ ሂደቶች የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ ሊጉ ሲጀምር ግን የተቋሙ ሎጎ አለመኖሩን ከ18ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ አሁን ግን ሎጎው ዳግም መመለሱን ለማወቅ ችለናል።
ጉዳዩን ለማጥራት ጥረት ብናደርግም ተጨባጭ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖሩ ምላሾች እና ማብራሪያዎች ካሉ ግን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።
ዘንድሮ ሊጉ ሲጀምር ከተደረጉ ጨዋታዎች አንዱ የቀጥታ ስርጭቱ የውጤት ማሳያ 👇
በአሁኑ ሰዓት እየተደረጉ ከሚገኙ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የቀጥታ ስርጭት የውጤት ማሳያ 👇