ምዓም አናብስቱ ቢጫዎቹን ሁለት ለአንድ በመርታት በሊጉ የሚቆዩበትን ዕድል አለምልመዋል
ወልዋሎ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ማጌ አለም በሳሙኤል ዮሐንስ እና ስምዖን ማሩ ተክተው ሲገቡ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ መድሀኔ ብርሀኔ እና ቦና ዐሊ በሰለሞን ሀብቴ እና አሸናፊ ሀፍቱ ተክተው ገብተዋል።
በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች ያልደመቐ ሲሆን ወልዋሎዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በተጠጋ አቀራረብ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት እንዲሁም መቐለ 70 እንደርታዎች ደግሞ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር።
በአጋማሹ በአመዛኙ ወደ መከላከል ያዘነበለ አቀራረብ በነበራቸው ወልዋሎች በኩል ሳሙኤል ዮሐንስ ከቆመ ኳስ ቀጥታ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣት ኳስ ብቸኛው ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። እንዲሁም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጎብኘት የተሻሉ በነበሩት መቐለ 70 እንደርታ በኩል ያሬድ ብርሀኑ ከግቡ አቅራብያ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ናትናኤል ኪዳነ እንደምንም ወደ ውጪ ያወጣት እና ሄኖክ አዱኛ ከመአዝን አሻምቷት ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ያደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ በአጋማሹ የታዩ ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በአጋማሹ የመጠናቀቅያ ደቂቃዎች ላይ ሰሎሞን ሐብቴ አሻምቷት ቤንጃሚን ኮቴ በግንባር ሞክሯት ናትናኤል ኪዳነ በእግሩ ያወጣት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራም መቐለዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ መቐለ 70 እንደርታዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ሁለተኛው አጋማሽ ምዓም አናብስት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመያዝ በተሻለ ድፍረት ለማጥቃት የጣሩበት ሲሆን ወልዋሎዎች ግን የአቀራረብ ለውጥ ሳያደርጉ በአመዛኙ ወደ መከላከሉ ባዘነበለ አጨዋወት በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም መቐለ 70 እንደርታዎች ከሰለሞን ሐብቴ መነሻቸው ባደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገው ሙከራዎች ሳያከናዉኑ ከቆዩ በኋላ በ ሀምሳ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከግቧ መቆጠር ቀደም ብሎ ሙልጌታ ላደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ አመቻችቶ ያቀበለው ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን አሻግሯት ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ ከመረብ ጋር ያዋሃዳት ኳስም ምዓም አናብስቱን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሽግግሮች እና በመልሶ ማጥቃቶች በተሻለ መንገድ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ወልዋሎዎች ጥረታቸው ሰምሮ በ83′ ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር የቻሉ ሲሆን ናትናኤል ሰለሞን ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት በሶፎንያስ ሰይፈ ጥረት መዳን ያልቻለችው ኳስም ቢጫዎቹን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ነበረች።
ሆኖም የአቻ ውጤቱ ለሦስት ደቂቃዎች ብቻ የቆየ ነበር፤ በ86′ ደቂቃም ምዓም አናብስት በሰለሞን ሃብቴ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ሄኖክ አዱኛ አሻግሯት ሰለሞን ሀብቴ ያስቆጠራት ጎልም የማታ ማታ መቐለን አሸናፊ ያደረገች ወሳኝ ግብ ሆናለች።
መቐለዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወልዋሎዎች በተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ብያደርጉም ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቋል። ይህንን ተከትሎ በጊዝያዊነትም ቢሆን መቐለ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት የመትረፍ ዕድላቸውን አለምልመዋል።