አሠልጣኞቹ ከፌዴሬሹኑ የበላይ አካል ጋር ውይይት አድርገዋል

አሠልጣኞቹ ከፌዴሬሹኑ የበላይ አካል ጋር ውይይት አድርገዋል

ከሰሞኑ ክለቦች ለ2018 የውድድር ዘመን ሊያሟሏቸው በሚገቡ መስፈርቶች ዙርያ ግርታ ፈጥሮብናል ያሉ የC ላይሰን ያላቸው አሰልጣኞች ወደ ፌዴሬሽኑ ቢሮ በመሄድ የበላይ አካላቶችን አናግረው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

የሀገሪቱን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ የተለያዩ ውሳኔዎችን መወሰኑ አይዘነጋም። የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት በዋናነት ከወሳኗቸው ውሳኔዎች መካከል በፕሪምየር ሊጉ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ከቀጣዩ የውድድር ዘመን ጀምሮ የካፍ የኤ ላይሰንስ ብቻ ሊኖራቸው ይገባል የሚል ይገኝበታል። ነገር ግን ለ2018 ብቻ የቢ ላይሰንስ ፍቃዳቸውን ተጠቅመው ማሰልጠን ይችላሉ በሚል ያወጣውን መመሪያ በርካቶች በፕሪምየር ሊጉ ላይ በዋና አሰልጣኝነት እና በረዳት አሰልጣኝነት እያገለገሉ ያሉ የቢ እና የሲ ላይሰንስ በያዙ አሰልጣኞች ዘንድ ውሳኔው ምንም ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ፣ አስቀድሞ የተመቻቸ ስልጠና ሂደት ሳይዘጋጅ ድንገት የተወሰነ ውሳኔ ነው በሚል ግርታ ተፈጥሯል ሲባል ተሰምቷል።

በዚህ ውሳኔ ሰለባ የሆኑ በአሁኑ ወቅት ከፍ ባለ የሊጉ ዕርከን በማሰልጠን እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ከአስር በላይ የሚጠጉ አሰልጣኞች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለመነጋገር በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ወደ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በመሄድ ውይይት ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

በውይይቱ ወቅት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በንግግራቸውም “ያለፉት ዘጠኝ ዓመታት በስልጠናው የራሳቸውን አሻራ ሲያሳርፉ እንደቆዮ እና በዚህ የዘጠኝ ዓመት ቆይታ ውስጥ የቢ ላይሰንስ ስልጠናውን ለመውሰድ ቢፈልጉም ስልጠናው የተዘጋጀው በቅርቡ መሆኑ እና ስልጠናውን የሚወስዱት ሰልጣኞች የአወሳሰድ ቅድመ ተከተል መስፈርት አወጣጥ ግልፅ አለመሆኑ ላይሰንሱን ለማግኘት እንዳስቸገራቸው ተናግረው ፌዴሬሽኑ ይሄንን ከግምት አስገብቶ ጉዳዮን በትኩረት እንዲያጤነው ጠይቀዋል። የፌዴሬሽኑ የበላይ አካላትም በምላሻቸው ውሳኔው ከካፍ በአስገዳጅ ሁኔታ የመጣ ትዕዛዝ በመሆኑ ምንም ዓይነት የመስፈርቶቹ ማሻሻያ ለውጥ እንደማይኖር መግለፃቸውን አውቀናል። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ጥያቄያቸውን በትኩረት እንደሚያየው እና በቅርብ ቀናት ውስጥ የማሻሻያ እና የላይሰንስ ዕድገታቸውን ከፍ የሚያደርጉ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ እንደሚያመቻችላቸው ምንጮቻችን ጠቁመውናል።