👉”ብሔር እና ፓለቲካ ውስጥ ራሳቸውን ደብቀው እግርኳስ እንዳይመስል የሚያደርጉ ክለቦችን እና አመራሮች አሉ።”
👉”ዕከሌ ቡድን ተሸነፈ ሲባል ቀጥታ ከብሔር እና ከማንነት ጋር ማያያዝ በእግርኳስ ውስጥ..”
👉”እግርኳስ ከዘር እና ከፖለቲካ የፀዳ ሊሆን ይገባል።”
👉”በቁርጠኝነት ይሄን ለማስፈፀም ይሰራል።”
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞን የተለያዩ አለም አቀፍ የእግርኳስ መርህዎችን በተከተለ እና ከፊፋ በመጡ ግፊቶች መነሻነት የተለያዮ ሊሟሉ በሚገቡ ጉዳዮችን ዙርያ ትዕዛዞችን እያስተላለፈ ይገኛል። ከነዚህም መካከል በትናትናው ዕለት ክለቦች ለአዲሱ የውድድር ዘመን ምዝገባ ለመመዝገብ ሲመጡ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶች አንዱ ነው።
ፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀው ከሆነ የክለብ ስያሜያቸው ከብሔር ስም ጋር የሚገናኝ ከሆነ ማስቀየር እንዳለባቸው እንዲሁም በክለቦቹ ይፋዊ መለያ(አርማ) ላይ ፓለቲካዊ እና የብሔር ይዘት ያላቸው መልዕክቶች እና ምስሎች መጠቀም የተከለከለ መሆን አሳውቋል። በዚህ መነሻነት ደንቡ የወጣበት ምክንያት እና ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ የፌዴሬሽኑ ቁርጠኝነት እስከምን ድረስ ነው ስንል የፌዴሬሽኑን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁንን አናግረን ተከታዮን ምላሽ ሰጥተውናል።
“እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ ደንብ አይደለም ያወጣነው። በደንባችን ላይ ያለ እንደዚሁም በፊፋ አና በካፍ መተዳደርያ ደንብ ላይ የተቀመጠ ነው። እግርኳስ ከዘር እና ከፖለቲካ የፀዳ ሊሆን ይገባል። በዚህ ዓይነት መሰል ስያሜ የመጡ ክለቦች ራሳቸውን ሊያስተካክሉ እንደሚገባ የተቀመጠ ደንባችን ላይ ያሰፈርነው ፊፋም በየጊዜው የሚገልፀው ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ይህንን ለክለቦች እንዲያውቁት ያሳወቅነው።
“ወቅቱ የክለቦች ምዝገባ የሚደረግበት ስለሆነ ይህንን ነገር አስተካክለው እንዲመጡ የማድረግ፣ የማሳወቅ ስራ ነው የተሰራው። ስለዚህ ክለቦች ራሳቸው አስተካክለው መምጣት አለባቸው። ክለቦች ራሳቸውን በዘር እና በፖለቲካ ስያሜ(አርማ) ያላቸውን ማስተካከል አለባቸው። እኛ የምንመራው የምናስተዳደረው እግርኳስ ነው። ከእግር ኳስ ያለፈ አይደለም ነገር ግን ብሔር እና ፓለቲካ ውስጥ ራሳቸውን ደብቀው እግርኳስ እንዳይመስል የሚያደርጉ ክለቦችን እና አመራሮች አሉ።
“ዕከሌ ቡድን ተሸነፈ ሲባል ቀጥታ ከብሔር እና ከማንነት ጋር ማያያዝ በእግርኳስ ውስጥ ከዚህ ቀደም የነበረ ነገር ነው። እኛ ደግሞ ይሄን ማከም አለብን። በእግርኳስ ማደግ ፣የተሻለ የአስተዳደር ነገሮች እንዲኖር ከፈለግን የወጡ ህጎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ማድረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ግዴታ አለበት። ስለዚህም በፊፋ እና በካፍ እንዲሁም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መተዳደርያ ደንብ መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ በሰርኩላር መልክ አሳውቀናል።
“ከዚህ ቀደም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ተቸግረን የነበርነው ክለቦች ምዝገባ ካደረጉ በኋላ ነበር ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሮ የነበረው። አንድ ክለብ አስታውሳለው ወድያውኑ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሰረት የስያሜ ለውጥ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ‘የክለቡ አመራር ፍላጎት እንጂ ክለቡ አይደለም’ ብለው አመራሩን እስከማንሳት የደረሱበት እንደነበረ አስታውሳለው። ስለዚህ በእኛ የማስፈፀም ክፍተት የሚሰዋ አመራር ወይም ወደ ጎን ሊደረግ የሚገባ አካል ሊኖር አይገባም። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቁርጠኝነት ይሄን ለማስፈፀም ይሰራል። ለተግባራዊነቱ ክትትል እናደርጋለን ፤ አልፎ ተርፎም ማጣራቶችን እናደርጋለን። ይህ አዲስ ውሳኔ አዲስ የመጣ ነገር አይደለም። እግርኳሱ ላይ አዲስ የመጣ ሀሳብ አይደለም።” በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል።