ብሔራዊ ቡድኑ አሜሪካ ከገባ በኋላ ሁለተኛ ልምምዱን ሲሰራ ሱራፌል ዳኛቸው እስካሁን ልምምድ አለመስራቱ እና ከስብስቡ ውጭ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ነገ በሀገረ አሜሪካ ለሚያደርገው የኢግዚቢሽን ጨዋታ የሀገር ቤት ዝግጅቱን አጠናቆ ባሳለፍነው ማክሰኞ ወደ ስፍራው ማቅናቱ አይዘነጋም። በዋሺንግተን ዲሲ ቢልቮየር ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት የልምምድ ቀናቶችንም አሳልፏል።
የቡድኑን ስብስብ በዛው በአሜሪካ የሚቀላቀሉት ከንዓን ማርክነህ እና ሱራፌል ዳኛቸው በተጠበቀው መሠረት አጥቂው ከንዓን ቡድኑን በመቀላቀል የሁለት ቀን ልምምዶቹን በአግባቡ መስራቱን ሲታወቅ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ግን ሁለቱን ቀን ልምምዱን አለመስራቱን ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ሱራፌል የመጀመርያውን ልምምድ ከቡድኑ ጋር ያልተገኘ ሲሆን ትናንት ግን ቡድኑን መቀላቀሉን ቢታወቅም ልምምድ አለመስራቱ ታውቋል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማቀወቅ ባደረግነው ማጣራት ሱራፌል ብሔራዊ ቡድኑ ከተጠራ በኋላ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት እንዳጋጠመው አውቀናል። ይህን ተከትሎ ሱራፌል ነገ ከሚኖረው ጨዋታ ከስብስቡ ውጭ መሆኑን አረጋግጠናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ 20ሺህ ተመልካች በሚይዘው አውዲ ፊልድ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል።