ቅድመ ክፍያ የፈፀመ ክለብ የሚቀጣው ቅጣት ምንድን ነው?

ቅድመ ክፍያ የፈፀመ ክለብ የሚቀጣው ቅጣት ምንድን ነው?

አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ያደረገው የሊጉ አክስዮን ማኀበር ቅድመ ክፍያ የፈፀመ ክለብ የሚቀጣው ቅጣት የተደረገበትን የተሻሻለውን ውሳኔ ሶከር ኢትዮጵያ መረጃውን አግኝታለች።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሰባተኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በካፒታል ሆቴል የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዘለግ ላሉ ሰዓታት አካሂዷል። ጉባዔው ላይ ከተነሱት ሁለት አጀንዳዎች መካከል አስቀድመን ባጋራናችሁ መረጃ መሠረት አንደኛው የ2018 የጥቅል ክፍያ ጣሪያ ላይ በክለብ 70,000,000.00 (ሰባ ሚሊዮን ብር) እንዲሆን በአብላጫ ድምፅ እንደፀደቀ ይታወቃል።

ሁለተኛው ደግሞ በክለቦች ብዙ ጊዜ ወስዶ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ክለቦች ክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ማሻሻያ አንዱ ነበር። በተለይ የፋይናስ ስርዓቱን መመርያ የተከለከለውን የቅድመ ክፍያ ደሞዝና ፊርማ የከፈለ ክለብ ቅጣት ውሳኔ ማሻሻያ እንደተደረገባቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ለአብነት ያህል አንቀጽ 15 ላይ ተደንግጎ የነበረው “የቅድመ ክፍያ ደመወዝና ፊርማ መክፈል በአንቀጽ 6 ንዑስ 4 የተከለከለውን የቅድመ ክፍያ ደመወዝና ፊርማ የከፈለ ክለብ በሚከተለዉ አግባብ ይቀጣል፡፡

1) ድርጊቱ ለአንድ የቡድን አባል ከሆነ ስፖርት ክለቡ 5 ነጥብ ቅነሳ እና የ1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) ቅጣት ፣ ለክለቡ ሥራ አስኪያጅ እና ፕሬዚዳንት ከፍተኛ አመራር የፅሁፍ ማሰጠንቀቂያ ይሰጣል። የቅጣቱን ገንዘብ እንዲከፍሉ ደብዳቤ በደረሳቸዉ በ7 ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማህበሩ ገቢ ማድረግ አለባቸዉ። ከ7 ቀናት በኃላ ገቢ ካላደረገ 0.1% ወለድ ታሳቢ በማድረግ በ30 ቀናት ማስገባት አለባቸዉ፡፡ 30 ቀናት ካለፉ ግን ከውድድር ይሰረዛል።

2) ድርጊቱ ከአንድ አባል በላይ ወይም ለሁለተኛ ጊዜ ተፈፅሞ ቢገኝ ክለቡ በውድድር ዓመቱ ተጫዋች ዝውውር እንዳያደርግ ፣ ለእያንዳንዱ ድርጊት /የቡድን አባል/ የ5 ነጥብ ቅነሳ፣ የ1,000,000.00 (አንድ ሚሊዮን ብር) ቅጣት ይከፍላል፣ በወቅቱ የነበሩት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ፣ እና ፕሬዚዳንት/ ወይም ከፍተኛ አመራር/ ለሁለት የውድድር ዘመን ከማንኛውም ክለብ አመራርነት እንዳይሳተፉ ይታገዳሉ። የቅጣቱን ገንዘብ እንዲከፍሉ ደብዳቤ በደረሳቸዉ በ7 ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማኅበሩ ገቢ ማድረግ አለባቸዉ። ከ7 ቀናት በኃላ ገቢ ካላደረገ 0.1% ወለድ ታሳቢ በማድረግ በ30 ቀናት ማስገባት አለባቸዉ። 30 ቀናት ካለፉ ግን ከውድድር ይሰረዛል።

3) ክፍያውን የተቀበለው የክለብ አባል ድርጊቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈጸመ የ 7(ሰባት) ጨዋታ እገዳ እና 500,000.00 (አምስት መቶ ሺ ብር) ቅጣት ይተላለፍበታል። ቅጣቱን ዉሳኔዉ በደረሰዉ 7 ቀናት ዉስጥ ገቢ ማድረግ አለበት። ከሰባት ቀን በኋላ ቅጣቱን ገቢ እስኪያደርግ ድረስ ከውድድር
ይታገዳል።

4) ተቀባዩ ድርጊቱን የፈጸመው ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ ለሁለት አመት በሊጉ ውስጥ ከማንኛውም ዓይነት ውድድር እገዳ ይጣልበታል።

* ይህ መነሻ ሀሳብም በቀጣይ በጉባዔው ላይ ጸድቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ይጠበቃል። ሶከር ኢትዮጵያም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል።