ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አሜሪካ በማምራት ከዲሲ ዩናይትድ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ አራት ተጫዋቾቹ የሙከራ ዕድል ማግኘታቸው ተሰምቷል።
በዲሲ ዩናይትድ እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መካከል በተደረገው የሦስት ዓመት ስምምነት መሰረት ዋልያዎቹ ወደ ሀገረ አሜሪካ አምርተው የነበረ ሲሆን ባሳለፍነው ቅዳሜም በአውዲ ፊልድ ቡድኖቹ የወዳጅነት ጨዋታ አከናውነዋል። በጨዋታው ዙሪያ በሁለት ጎራዎች የተለያዩ ሀሳቦች እየተሰጡ የሚገኙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ስፍራው ካመሩ ተጫዋቾች መካከል አራቱ ጨዋታውን በተመለከቱ መልማዮች ዐይን ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል።
በዚህም ከነዓን ማርክነህ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ቢኒያም በላይ እና ራምኬል ጀምስ የመልማዮች ራዳር ውስጥ የገቡ ሲሆን ምናልባት ነገ ከሰዓት ወደ ሀገሩ ከሚመለሰው ልዑክ ጋር አብረው ሊመለሱ እንደማይችሉ ተገልጿል።
የብሔራዊ ቡድኑን የአሜሪካ ቆይታ በተመለከተ ከሰዓታት በኋላ አሜሪካ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ያገኘነው መረጃ ሲያመለክት የተጫዋቾቹ ጉዳይ ላይም ማብራርያ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።