የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቶታል፡፡ መከላከያ ከ ዳሽን ቢራ ካለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በ09፡00 ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ የባንክን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ተቀይሮ ለመውጣት በመዘጋጀት ላ የነበረው ሲሳይ ቶሊ ነው፡፡ ሲሳይ በ70ኛው ደቂቃ ላይ ግቧን አስቆጥሮ በ30 ሴኮንዶች ውስጥ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡
ሀዋሳ ከተማዎች በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሙሉጌታ ምህረት መትቶ በፌቮ ኢማኑኤል ተመልሶበታል፡፡
በ11፡30 ዳሽን ቢራን ያስተናገደው መከላከያ ካለግብ ጨዋታውን አጠናቋል፡፡ ጨዋታው ወጥ ያልሆነ እንቅስቃሴ ፣ እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና የሀይል አጨዋወቶች ከማስተናገዱ ውጪ ለተመልካች እጅግ አሰልቺ ነበር፡፡
በ18ኛ ሳምንት ከተደረጉት 7 ጨዋታዎች ሶስቱ ካለግብ ሲጠናቀቁ በአጠቃላይ የተቆጠሩት ግቦች ብዛት 6 ብቻ ነው፡፡ ሊጉ የፉክክር መጠኑ እንዲያድግ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት በግብ ድርቅ ክፉኛ መመታቱ እና በአሰልቺ ጨዋታዎች መታጀቡ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
የሊጉ ቡድኖች በተለይም ከሜዳቸው ውጪ የሚጫወቱ ቡድኖች ግብ እንዳይቆጠርባቸው በሙሉ ሃይላቸው መከላከልን በማለም ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡
የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ፕሮግራም
አርብ ግንቦት 5 ቀን 2008
09፡00 ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሆሳዕና)
09፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ድሬዳዋ)
09፡00 ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ይርጋለም)
09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ (ሀዋሳ)
09፡00 ዳሽን ቢራ ከ አዳማ ከተማ (ጎንደር)
09፡00 አርባምንጭ ከተማ ከ ኤሌክትሪክ (አርባምንጭ)
11፡30 ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ቡና (አአ ስታድየም)