ነገ ወደ ካይሮ ከሚያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን አባላት መካከል ሁለት ተጨዋቾች ከስብስብ ውጭ እንደሆኑ ተረጋግጧል።
ከግብፅ እና ሴራሊዮን ጋር ለሚያደርጓቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ለ26 ተጨዋቾች ጥሪ በማድረግ ከቀናት በፊት ዝግጅት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ኪቲካ ጅማ በግል ጉዳይ ምክንያት አስቀድሞ ከስብስቡ ውጭ መሆኑ ይታወሳል። አሁን ደግሞ አጥቂዎቹ አህመድ ሁሴን እና ቢንያም ዐይተን ከስብስብ ውጭ መሆናቸውን አረጋግጣለች።
ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ሁለቱ አጥቂዎች ትናት ከቡድኑ እንደተቀነሱ ከሆቴል እንደወጡ እና በዛሬው የዕረፋድ ልምምድ አሰልጣኝ መሳይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ በአዲስ አበባ ስታዲየም እያሰሩ እንደሆነ ታውቋል።
ነገ ረፋድ ላይ የመጨረሻ ልምምዱን የሚሰራው ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቀትር ላይ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ አመሻሽ ላይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ካይሮ የሚያቀና ይሆናል።