በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በወልዋሎ ቆይታ የነበረው አጥቂ አዲስ አዳጊውን ለመቀላቀል ተስማማ።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ለ’ በ 47 ነጥብ በአንደኝነት ካጠናቀቁ በኋላ በፍፃሜው ጨዋታ የምድብ ‘ሀ’ በአንደኝነት ያጠናቀቁትን ሸገር ከተማዎችን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ የ2017 የከፍተኛ ሊግ አሸናፊ የሆኑት ነገሌ አርሲዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከዳዊት ተፈራ ቀጥሎ ሁለተኛ ፈራሚያቸውን ለማግኘት ተስማምተዋል። ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ደግሞ ተስፈኛው አጥቂ ናትናኤል ሰለሞን ነው።
በተጠናቀቀው ዓመት የወልዋሎ ቆይታው በ20 ጨዋታዎች ተሳትፎ 989′ ደቂቃዎች ቡድኑን በማገልገል አራት ግቦችን ያስቆጠረው ወጣቱ ተጫዋች ከዚህ ቀደም በመቻል ወጣት ቡድን፣ በከፍተኛ ሊጉ ንብ እንዲሁም ከሀያ ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት የወልዋሎ ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ ለማምራት ተስማምቷል።