ጌታነህ ከበደ አዲስ ክለብ ለማግኘት ከጫፍ ደርሷል

ጌታነህ ከበደ አዲስ ክለብ ለማግኘት ከጫፍ ደርሷል

ወደኢትዮጵያ ቡና ለማምራት ጠንከር ያለ ንግግር ላይ የነበረው ጌታነህ ከበደ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል።

ከሚሊንየም በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው አጥቂው ጌታነህ ከበደ ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረው ቆይታ መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣይ ማረፊያው የት ይሆናል በሚል ዙርያ አንድ ዘገባ መስራታችን ይታወቅ ነበር። ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሊያመራ እንደሚችል ከምንጮቻችን ያገኘነውን መረጃ ተንተርሰን ዘገባ ብናቀርብም የዝግጅት ክፍላችን አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ለሚሰለጥነው ሀዋሳ ከተማ ለመፈረም የተስማማ ሲሆን የህክምና ምርመራውን ዛሬ እያደረገ እንደሆነ አውቀናል።

የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ ደደቢት፣ የደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድ ዌስት ክለብ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ከደቡብ አፍሪካ ዳግም በመመለስ ደደቢትን በድጋሚ ተቀላቅሎ ከተጫወተ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልቂጤ ከተማ ካሳለፈ በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በዐፄዎቹ ቤት ቆይታ ሲያደርግ አሁን ማረፊያው ኃይቆቹ ቤት ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ2003 በ2005 እና በ2009 ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እንዲሁም 2001 እና 2005 ኮከብ ተጫዋች በመሆን ያጠናቀቀው ጌታነህ በብሔራዊ ቡድን ረጅም ዓመት አብሮት ከተጣመረው ሽመልስ በቀለ ጋር በሀዋሳ ከተማ ማልያ የሚጣመሩ ይሆናል።