በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን ወደ እንግሊዝ ክለቦች ለማምራት ከጫፍ ደርሶ የነበረው ተጫዋች ማረፍያው ‘UAE Pro League’ ሆናል።
በቅርብ ዓመታት በአውሮፓ ምድር ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንዱ የሆነው ሀሩን ኢብራሂም ወደ ኢንግሊዝ ክለቦች ሊያደርገው የነበረው ዝውውር በመጨረሻው ሰዓት ከከሸፈ በኋላ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቱ ክለብ ሻርጃህ አምርቷል። በዝውውር መስኮቱ መዝጊያ ቀን ላይ በእንግሊዝ ቻምፒዮን ሺፕ ተሳታፊ ለሆኑት ኪው ፒ አር እና ኦክስፎርድ ለመዘዋወር ከጫፍ ደርሶ የነበረው ይህ አማካይ ከዓመታት የስዊድኑ ክለብ ጋይስ ቆይታ በኋላ ወደ ሻርጃህ ፊርማውን አኑሯል።
እንደ ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ክሪስቶፈርሰን
እንዲሁም ‘Expressen’ ዘገባ ከሆነ ከሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች በተጨማሪ የስኮትላንዱ ሬንጀርስ እና የጀርመኑ ኑረንበርግ ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ለማዘዋወር ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ወደ 10 ሚሊዮን ክሮነር ከፍ ሊል በሚችል 7.5 ሚሊዮን ክሮነር በሦስት ዓመት ውል በቀድሞ
Hammarby፣ Mjällby እና Malmo አሰልጣኝ ሚሎስ ሚሎጄቪች ወደ ሚሰለጥነው ሻርጃህ ለማምራት ፊርማውን አኑሯል።
ሀሩን ኢብራሂም ከዚህ ቀደም በአሳዳጊ ክለቡ ‘GAIS’ በሦስት አጋጣሚ እንዲሁም የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ባገኘበት የኖርወዩ ‘Molde’ እንዲሁም በስዊድኑ ‘Sirius’ መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት በ’UAE Pro League’ 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀውና ሁለተኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው አዲሱ የውድድር ዓመት 5ኛ ደረጃ ላይ ወደ ተቀመጠው ሻርጃህ አምርቷል።