ቁመታሙ የመሃል ተከላካይ ሰጎኖቹን ተቀላቅሏል

ቁመታሙ የመሃል ተከላካይ ሰጎኖቹን ተቀላቅሏል

በአውሮፓ ፣ አሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ የተለያዩ ክለቦች ቆይታ የነበረው የመሃል ተከላካይ አዲስ አዳጊውን ክለብ ተቀላቅሏል።

በሊጉ ታሪክ የመጀመርያ ተሳትፏቸውን ባሳለፍነው ቅዳሜ አከናውነው በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት አዲስ አዳጊዎቹ ነገሌ አርሲዎች ሁለተኛ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ካሜሮናዊ ተከላካይ አስፈርመዋል።

በካሜሮን ኢቦሎዋ የተወለደው እና 1.93 ሜትር የሚረዝመው ቁመተ መለሎው የመሃል ተከላካይ ፓስካል ኢቦውሲ የእግርኳስ ጅማሮውን በሀገሩ ክለብ ሬንቦው አድርጎ ከዛም ወደ አሜሪካ ሁለተኛ ዲቪዚዮን አቅንቶ ለስዊችባክስ የተጫወተ ሲሆን በሦስት አጋጣሚዎች በየአንድ ዓመት ልዩነት ለቼክ ሪፐብሊኩ ቪሽ ኮቭ ካደረጋቸው ቆይታዎች መሃል ለአሜሪካው ሳን አንቶኒዮ እና ለስዊድኑ አይኤፍኬ ሎሊኦ ፈርሞ አንድ አንድ ዓመት ቆይታ ሲያደርግ በመቀጠልም ለሱዳኑ ኤል ሜሪክ እና ለግሪኩ ፓይሪኮስ ግልጋሎት ሰጥቷል።


በመጨረሻም ለአንድ ዓመት ያህል ያለ ክለብ ከቆየ በኋላ ባለፈው ዓመት በዲሞክራቲክ ኮንጎው ቪታ ክለብ ለሦስት ዓመታት ለመቆየት ፊርማውን ቢያኖርም ሁለት ቀሪ ዓመታት እየቀሩት በስምምነት በመለያየት አሁን መዳረሻውን የኢትዮጵያውን ክለብ ነገሌ አርሲ አድርጓል።