የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት መጠናቀቂያ ቀን ላይ አዳማ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
አዳማ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከኢትዮጵያ መድን እና ከሸገር ከተማ ጋር በተመሳሳይ የባዶ ለባዶ ውጤት ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ነብሮቹን ይገጥማሉ። አዳማ ከተማዎች በሁለቱም መርሐግብሮች መረባቸውን ባለማስደፈር በመከላከሉ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በዛሬው ጨዋታም የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።
በባህርዳር ከተማ ሽንፈት አስተናግደው ዓመቱን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻው ጨዋታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተው የመጀመርያው ነጥብ ካሳኩ በኋላ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ነብሮቹ ሦስት ግቦች ካስተናገዱበት ጨዋታ በኋላ በመከላከሉ ረገድ ውስን መሻሻል አሳይተው በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ መረባቸውን አስከብረው መውጣት ቢችሉም የማጥቃት አጨዋወታቸው ግን አሁንም መሻሻል የሚገባው ነው።
በአዳማ በኩል ቢኒያም ዐይተን ፣ ማይክል ኪፕሩቪ፣ ማይክል ሰፋ፣ ሚራጅ ሰፋ፣ አላዛር ሽመልስ በጉዳት እና በህመም ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን የነቢል ኑሪ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ኤልያስ አሕመድ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 12 ጊዜ ተገናኝተው ሀዲያ ሆሳዕና 5 ጊዜ፤ አዳማ ከተማ ደግሞ 4 ጊዜ ሲያሸነፉ 3 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። አዳማ 12 ሀዲያ ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
በሀዋሳ ከተማ የሁለት ለባዶ ሽንፈት አስተናግደው ውድድር ዓመቱን የጀመሩት እና በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ላይ ድል አድርገው ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ መቐለ 70 እንደርታን ይገጥማሉ። ብርቱካናማዎቹ ከሽንፈት መልስ መረባቸውን አስከብረው በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የጦና ንቦቹን ማሸነፍ ቢችሉም አሁንም የኋላ ክፍላቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።
በምድረገነት ሽረ ሽንፈት አስተናግደው ውድድር ዓመቱን ከጀመሩ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ከመቻል ጋር ነጥብ የተጋሩት መቐለ 70 እንደርታዎች የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጀመርያው አጋማሽ ደካማ አጀማመር ማድረግ በምዓም አናብስት በኩል የሚጠቀስ ድክመት ነው። ግብ አስቆጥረው ነጥብ በተጋሩበት ጨምሮ በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሻለ ብቃት ያሳየው ቡድኑ በነገው ጨዋታ አጀማመሩን ማሻሻል ግድ ይለዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ልምምድ ላይ ላይ በገጠመው ጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩልም ግብ ጠባቂው ሐድሽ በርኸ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን 7 ጊዜ ሲገናኙ ምዓም አናብስት 4 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ሲይዙ ብርቱካናማዎቹ በአንፃሩ 2 ድል አድርገው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።በግንኙነታቸውም ሞዓም አናብስቱ 10 ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው 7 ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።


