በቅርቡ ወላይታ ድቻን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የተረከቡት ምክትል አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር እንደማይገኙ ታውቋል።
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ በሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ከዋና አሰልጣኙ ጋር መለያየቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ምክትል አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ቀነኒ በጊዜያዊነት ቡድኑን እንዲመሩ መደረጉም ይታወሳል።
በአምስተኛ ሳምንት ቡድኑን በጊዜያዊ አሰልጣኙ እየተመራ ከአራት ጨዋታ በኋላ አንድ ነጥብ ያስገኙት አሰልጣኝ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ዋንጫ ትናንት ወላይታ ድቻ በወልዋሎ ተረቶ ከውድድሩ ውጭ በሆነበት ጨዋታ ላይ ቡድኑን ጥለው መሄዳቸውን አረጋግጠናል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው አሰልጣኝ ቴዎድሮስ “የክለቡ ኃላፊዎች መጀመርያ የሰጡኝን ኃላፊነት ተረክቤ ቡድኑን ጥሩ እየመራው ነበር። ሆኖም ከትናንትናው ጨዋታ አስቀድሞ ሌሎቹ የቡድኑ አሰልጣኝ አባላት ኃላፊነቴን ሊነጥቁኝ በማሰባቸው እና ሊያሰሩኝ በማለመቻላቸው ጥዬ ወጥቻለው በማለት” ሌሎች ችግሮችን በዝርዝር ነግረውናል።

በዚህም መነሻነት በትናንቱ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ የአካል ብቃት አሰልጣኙ አምጣቸው ኃይሌ ቡድኑን እንደመሩ ታውቋል። በዚህ ዘገባ ዙርያ የክለቡ ኃላፊዎች የሚሰጡት ምላሽ ካለ የምናቀርብ ይሆናል።
ሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እየታወከ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በቅርቡ የክለቡ የበላይ አመራሮች ምን አይነት ውሳኔዎች ይወስናሉ የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል።


