ፕሪምየር ሊጉ 11ኛ ሳምንቱ ላይ ደርሷል ፤ ነገርግን የሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠን 5 ብቻ ነው ታድያ ይህ ምን ይነግረናል?
የተወሰነ የይዘት(format) ማሻሻያ የተደረገበት የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመቱ ጉዞ ወደ ሲሶ የተጠጉ ጨዋታዎችን አስተናግዷል ፤ በተደረጉት 110 ጨዋታዎች ታድያ 200 ጎሎች ተቆጥረዋል ይህም በጨዋታ ከሁለት ጎል ያነሰ እንደማለት የመሆኑ ነገር ትኩረትን ይስባል።
ምን አልባት ይህን ቁጥር ይበልጥ ለመረዳት በሊጉ እስከ 11ኛ ሳምንት መገባደጃ የምርጡ ማጥቃት ባለቤት የሆነው መቻል 16 ግቦችን አስቆጥራል ይህም ማለት በጨዋታ 1.45 ግቦች እንደማለት ነው በተመሳሳይ በግለሰቦችን ደረጃ ስንመለከተው ከ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኃላ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎችን ዝርዝርንም ስንመለከት አዲስ ግደይ ፣ መሀመድ አበራ እና ያሬድ ብሩክ በአምስት ግቦች ሲመሩ አምስት ተጫዋቾች ደግሞ በጣምራ በአራት ግቦች ይከተላሉ።
እነዚህን ቁጥሮች በግርድፉ ለተመለከተ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ላይ ያለው የማጥቃት ጨዋታ እና አጥቂዎቻችን ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው ፤ ታድያ ይህ እውነታ ሊጉን በቅርብ ለሚከታተሉ ሰዎች የዘንድሮ ብቻ ሳይሆን የሊጋችን ያለፉት ጥቂት ዓመታት እውነታ እንጂ ፤ ለአብነት አምና ዓሊ ሱሌይማን በ18 ጎሎች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ በጨረሰበት የውድድር ዘመን ከ10 ግቦች በላይ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ብዛት ስድስት የመሆኑ ጉዳይ ሊጋችን ምን ያህል በጎል አስቆጣሪዎች እጥረት እየተጠቃ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
እርግጥ ግብ ማስቆጠር በተናጥል ለአጥቂዎች ብቻ የተሰጠ ተግባር ባለመሆኑ ችግሩን በቡድን መነፅር መመልከት ተገቢ ቢመስልም በዋነኝነት ግን ወደ ሜዳ ሲገቡ ዋነኛ ስራቸው ግብ ማስቆጠር በሆኑት አጥቂዎች ላይ ግን የበለጠ ትኩረት ማድረግ ይገባል።
ከዚህ ነባራዊ ሀቅ ጋር ተያይዞ ብዙ ጉዳዮችን በምክንያትነት ማቅረብ ቢቻልም በጥቅሉ ግን ግለሰባዊ እና የወል ምክንያቶች ብለን በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን ፤ እርግጥ ግለሰባዊ ምክንያቶች የወል ችግሮቹ ነፀብራቅ እንደሆነ ቢታመንም ሁለቱን ግን ነጣጥሎ መመልከት የግድ ይላል።

በጥቅሉ ሊጋችን ከጨዋታ መንገድ አንፃር ከአውንታዊ እግር ኳስ ይልቅ ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሰጠ አቀራረብ የበላይነቱን የያዘበት እንደሆነ ይታመናል ታድያ በዚህ መነሻነት ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ተጋጣሚ ሜዳ ላይ በመድረስ ግቦችን ለማስቆጠር ከመፈለግ ይልቅ የ0-0 ውጤትን ለማስጠበቅ አለፍ ሲልም የተገኘች ብቸኛ ግብን ለማስጠበቅ የሚታትሩ ቡድኖች አብዝተን የምንመለከትበት ነው በዚህም ቡድኖች በጨዋታ የሚፈጥሯቸው ዕድሎች ቁጥር አነስተኛ ነው በዚህም የሚቆጠሩትም ግቦች መጠን ያነሰ ያደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህን የሚፈጠሩ ውስን ዕድሎች እዚህ ጋር አብዛኛዎቹ ግማሽ ዕድሎች መሆናቸውን ከግምት በማስገባት የአጥቂዎቻችን የመጨረስ ብቃትም እንዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ፤ ከአጥቂዎቻችን የመጨረስ ብቃት ጋር ተያይዞ በየክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን እስካሁን የጎል አካውንታቸውን ያልከፈቱ በርካታ አጥቂዎች መኖራቸውን ለታዘበ ወደ የት እያመራን ነው ስንል እንዲጠይቅ ይገደዳል።
ይህ ችግር ታዲያ ብዙ ክለቦች በአጥቂ መስመር ላይ የሚሰለፉ በርካታ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው አጥቂዎችን ቢያስመጡም በአጥቂዎቹ ክለቦች የሚፈልጉትን ያክል እንዳልተጠቀሙ ግን እያስተዋልን እንገኛለን ፤ ግለሰቦች ተለዋውጠው ችግሩ ካልተፈታ የቡድኖችን የጨዋታ መንገድ አለፍ ሲልም የሊጋችንን ገዢ የጨዋታ ሀሳብ መፈተሽ ይኖርብናል ወደሚል ድምዳሜ ይመራናል።
ሊጋችን ግቦችን ለመመለከት ከሻተ ክፍት የሆኑ ጨዋታዎች ፣ አውንታዊ እግር ኳስ ገዢ ሀሳብ መሆኑ የግድ ይላል ይህ ካልሆነ ግን ግብ የሚያስቆጥሩ ክለቦች እና ለማስቆጠር የሚቸገር ብሔራዊ ቡድን ይዘን መጓዛችን የግድ ነው።
ጎሎች እግር ኳስን ህይወት ያላብሳሉ ፤ ታድያ በተመልካች ድርቅ ለተመታው ሊጋችን ጎሎች ተመልካቾችን ወደ ሜዳ መመለሻ ቁልፍ እንደሚሆኑ ይታመናል ታድያ ጎል በወጥነት የሚያመርቱ አጥቂዎች እና አግቢ ቡድኖችን መፍጠር የሊጋችን ቀጣዩ ብርቱ የቤት ስራ ነው።

