መጋቢት 18 እና 22 ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ያለበት ዋልያው 23 ተጫዋቾችን ከ12 የተለያዩ ክለቦች መርጧል። የትኞቹ ክለቦች ብዙ አስመረጡ?

አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ ታኅሣሥ 27 የዋልያዎቹ አለቃ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታቸውን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የሚያከናውኑ ሲሆን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ከደቂቃዎች በፊት ለጨዋታዎቹ የሚሆኑ 23 ተጫዋቾችን በበይነ መረብ ይፋ አድርጓል።
በዚህም ጋቶች ፓኖም እና ከነዓን ማርክነህ ከውጪ ሀገራት ክለቦች ጥሪ የደረሳቸው ተጫዋቾች መሆናቸውን እንዲሁም ግሩም ሀጎስ፣ ብዙዓየሁ ሰይፈ፣ ካቤ ብዙነህ እና ብሩክ እንዳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን በዋናው ብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንዲያገለግሉ ጥሪ እንደተደረገላቸው ዘገባ አቅርበናል።
አሠልጣኝ ዩሐንስ ሀያ ሦስቱን ተጫዋቾች ከ12 የተለያዩ ክለቦች የጠሩ ሲሆን ብዙ ተጫዋቾችን ከክለባቸው ያስመረጡትን እንደሚከተለው አስቀምጠናል።
የሊጉ መሪን ሲዳማ ቡና ጨምሮ መቻል፣ ኢትዮጵያ መድን፣ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ሦስት ተጫዋቾችን እኩል አስመርጠዋል። ከአምስቱ ክለቦች በመቀጠል ፋሲል ከነማ ሁለት ተጫዋቾችን ሲያስመርጥ ሀዋሳ ከተማ፣ ነገሌ አርሲ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እንዲሁም አል ሸባብ እና አል አረቢ አንድ አንድ ተጫዋቾችን አስመርጠዋል።

