አዞዎቹ አዳማ ከተማን 2-0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን አሳክተዋል

አርባምንጭ ከተማዎች ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን በ27ኛው ደቂቃም በጄሮም ፍሊፕ አማካኝነት መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግብ ጠባቂው አላዛር የሰራውን ስህተት ተከትሎ አሸናፊ ተገኝ ኳሱን በግንባሩ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው ወደ ግብነት በመቀየር ነበር አዞዎቹን መሪ ማድረግ የቻለው። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም በአዳማ ከተማ በኩል ቢኒያም አይተን እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ ኤፍሬም ታምራት ከቅጣት ምት የሞከሩት ሙከራ በግብ ጠባቂዎች ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን በማሻሻል ወደ ጨዋታ ለመመለስ ተደጋጋሚ ጫናዎችን መፍጠር የቻሉት አዳማ ከተማዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ብዙአየሁ ሰይፈ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል። ይህም ለአዳማዎች እጅግ አስቆጪ ሙከራ ነበር።
አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓትም አዞዎቹ ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። 62 ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባውና ቡድኑን ከተቀላቀለ ገና አንድ ሳምንት ያስቆጠረው ጋናዊው የ26 ዓመት ተጫዋች ዓብዱልራህማን መሐመድ ተቀይሮ በገባ በመጀመሪያ ንክኪው ተከላካዩን እንዲሁም ግብ ጠባቂውን በአስደናቂ ችሎታ በማለፍ በክለቡ የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን በአዞዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

