የሲዳማ ቡናው የፊት መስመር ተጫዋች የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደረሰው

በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ በአስራ ስምንት ጨዋታዎች በመሳተፍ 882′ ደቂቃዎች ቡድኑን ያገለገለው ፌድሪክ ኑሲ ሀገሩ የኢኳቶሪያል ጊኒ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች እንዲሳተፍ ጥሪ ደርሶታል። ሀገሪቱ ከባህሬን እንዲሁም ከማዳጋስካር ጋር በተርክዬ አንታልያ ከተማ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች የምታደርግ ሲሆን በሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና የሚጫወተው ፌድሪክ ኑሲ ደግሞ በጨዋታዎቹ ለመሳተፍ ጥሪ ደርሶታል።
ከዚህ ቀደም በሦስት አጋጣሚዎች ሀገሩን እንዲያገለግል ጥሪ የደረሰው ተጫዋቹ በመቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና ተጫውቶ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጓንቱን ከሰቀለው ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰው ሁለተኛ ተጫዋች ነው።

