“ልምድ እና ጫና የሚቋቋሙ ተጫዋቾችን መርጠናል” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ

“ልምድ እና ጫና የሚቋቋሙ ተጫዋቾችን መርጠናል” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ

👉 “ስም ሳይሆን አቅም ያለው ተጫዋች ገብቶ ይጫወታል።

👉 “እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ተጫዋቾቹ ያላቸውን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።”

👉 “በፋሲል ከነማ የምከተለው አጨዋወት እና ብሔራዊ ቡድን ሲሆን…”

የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳሕሌ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2027 አፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር ለሚያከናውነው የመጀመርያ ጨዋታ አስመልክቶ በቡድኑ ዝግጅት እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ በአሁኑ ሰዓት ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ ይገኛል። አሰልጣኙ ከመግቢያ ንግግራቸው በኋላ ስለሚከተሉት የጨዋታ መንገድ አስመልክቶ ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።

“የውድድሩ ዓላማ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ጥንቃቄ እንዲሁም ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ማካካተት ያስፈልጋል። በዚህ መነሻነት ልምድ ያላቸው እና ጫናን መቋቋም የሚችሉ ተጫዋቾችን መርጠናል ከዚህ ባሻገር የአካል ብቃት ወሳኝ በመሆኑ ምርጫችን ያንን መሠረት ያደረገ እንዲሆን አድርገናል። እንዲሁም አቅማቸውን ያሳዩ አንድ አንድ ወጣት ተጫዋቾችን መርጠናል ልምድ ባይኖራቸውም” ብለዋል። በመቀጠል “በተጫዋቾቹ በኩል ሁሉም በመልካም ጤንነት ናቸው በዲሲፒሊን ረገድ በጣም ጥሩ ነገርን አይተናል። ምንም ችግር አልተመለከትንም። እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ተጫዋቾቹ ያላቸውን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው። ይሄንን በልምምድ ሆነ በውይይት ወቅት ለሀገራቸውና ለባንዲራ አንድ ነገር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ማየታቸውን..” አፅኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

“አንድ ጨዋታ ሲሆን እና የዙር ጨዋታ ሲሆን ይለያያል። ፋሲል እከተለው የነበረው የመከላከል ጨዋታ እና እዚህ ብሔራዊ ቡድን ሲሆን የጨዋታው መንገድ ይለያያል በዚህ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጊዜ አይሰጥም ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታ ነው። ለዚህ ጨዋታ የሚሆን ዝግጅት አድርገናል። ባለችው አጭር ጊዜ ውስጥ ስህተቶችን እንዴት ቀንሰን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍን እንደሚገባን በስነልቦና ረገድም በአካል ብቃትም ሰርተናል።

እንዲሁም በጨዋታው ዕለት ስለሚጠቀሙት ቋሚ አስራ አንድ ሲናገሩ

“በስም አናምንም አቅም ያለው ተጫዋች ገብቶ ይጫወታል። እግርኳስ በወሬ አይደለም በሜዳ ላይ ያለውን የሰጠን ተጫዋች ይገባል” ብለዋል።