የመጨረሻ ልምምዱን እየሠራ በሚገኘው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ አንድ ተጫዋች አልተገኘም።

በ2027 ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ለማድረግ ከቀናት በፊት ዝግጅቱን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራው ቡድኑ ነገ ወደ ስፍራው ከማቅናቱ በፊት በአሁኑ ሰዓት የመጨረሻ ልምምዱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እየሠራ ይገኛል።
ሆኖም ከ23 ተጫዋቾች መካከል አንድ ተጫዋች በዛሬው ልምምድ አለመገኘቱን አረጋግጠናል።
ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል በኦማን ሊግ ስኬታማ ቆይታ እያደረገ የሚገኘው ከነዓን ማርክነህ ከቀናት በፊት የዋልያዎቹን ስብስብ በመቀላቀል ልምምድ እየሠራ ቢቆይም በዛሬው የመጨረሻ ልምምድ ላይ በሕመም ምክንያት አለመገኘቱን ለመመልከት ችለናል።
ከነዓን በምን ሕመም ምክንያት እንደቀረ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ከቡድኑ ጋር ነገ በሚደረገው ጉዞ አብሮ እንደሚሄድ አረጋግጠናል።

