ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት ቀጥለው ሲካሄዱ በአዲስ አበባ ስታዲየም ማምሻውን በተደረገው ጨዋታ በሊጉ ሁለተኛ ዙር በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር ደደቢትን 3-0 ረቷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ የጨዋታውን ታክቲካዊ ጉዳዮች እንደሚከተለው ታስቃኛለች፡፡
የቡድኖቹ ጨዋታ አቀራረብ
በያዝነው የውድድር ዓመት የቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፎች ላይ የፊት አጥቂነቱን ቦታ ይመራ የነበረውን ያቡን ዊልያምን በጉዳት ያጣው ኢትዮጵያ ቡና ትላንት ከፊት በጨዋታው ሀትሪክ የሰራውን ሳዲቅ ሼቾን አሰልፏል፡፡ እንዲሁም በተከላካይ አማካይነት እንደተለመደው ጋቶች ፓኖም ከተከላካዮች ፊት ተሰልፏል፡፡ ከጋቶች ፊት የነበሩት አማካዮች እንቅስቃሴ የቡድኑን ቅርፅ በ4-1-4-1 እና በ4-3-3 መካከል የሚዋልል እንዲሆን አድርገውታል፡፡ መስዑድ እና ኢልያስ በአብዛኛው ከጋቶች ፊት እና ከሳዲቅ ኋላ በነበረው ቦታ ላይ ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡
የሁለቱ የመስመር አማካዮች አማኑኤል ዮሐንስና እያሱ ታምሩ እንቅስቃሴ በተለይ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ከመሀል አማካዮቹ ተነጥለው በሳዲቅ ግራና ቀኝ በመገኘት የቡድኑን ቅርፅ ወደ 4-3-3 ያመዘነ እንዲሆን አድርገውት ነበር፡፡ በተጨማሪም በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃት ላይ ይሳተፉ የነበሩት የመስመር ተከላካዮቹ አህመድ ረሻድ እና የአብዱልከሪም መሀመድ እንቅስቃሴ ሲጨመርበት እያሱና አማኑኤል መስመሩን ለሁለቱ ተጨዋቾች በመተው አጥብበው ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ሲገቡ ቡድኑ ወደ 4-3-3 የቀረበ አጨዋወት እየተከተለ እንደነበር ለመመልከት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ መሀል ላይ ኳስ በሚያደራጅበት እንዲሁም ኳስ በደደቢት ቁጥጥር ስር በምትሆንበት አጋጣሚዎች አማኑኤል እና እያሱ ከመስዑድ እና ኤልያስ ጐን በመሆን ለኢትዮጵያ ቡና የ4-1-4-1 ቅርፅ ይሰጡት ነበር፡፡ በተለይ ቡድኑ በሚከላከልበት ወቅት ሁለቱ ተጨዋቾች በጥልቀት ወደኋላ በመመለስ በጋቶች ግራና ቀኝ ቦታ ላይ የሚኖረውን ክፍተት ተጋጣሚያቸው እንዳይጠቀምበት ጥረት ሲያደርጉም ተስተውለዋል፡፡
ጨዋታውን የጀመረበትን ቅርፅ ለመቀየር 30 ደቂቃዎች ብቻ የወሰደበት ደደቢት በመጀመሪያ ይዞት በገባው አሰላለፍ ዳዊት ፍቃዱን በብቸኛ የፊት አጥቂነት ሚና ሰጥቶት ነበር፡፡ ከዳዊት ጀርባ በሁለቱ መስመሮች የአምናው ኮከብ ግብ አግቢ ሳሙኤል ሳኑሚንና እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር ለቡድኑ መልካም እንቅስቃሴ ሲየደርግ የነበረውን ሽመክት ጉግሳን ከቡድኑ የጨዋታ አቀጣጣይ ሳምሶን ጥላሁን ግራና ቀኝ በማድረግ አሰልፏል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ ያሬድ ዝናቡን እና ብርሃኑ ቦጋለን ከተከላካዮቹ ፊት እና ከሶስቱ አማካዮች ጀርባ ባለው ቦታ ላይ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ነበር ጨዋታውን የጀመረው፡፡ በዚህም አኳኋን ደደቢት በ4-2-3-1 ቅርፅ ነበረው፡፡
ነገር ግን ቡድኑ በዚህ ቅርፅ የተጫወተው ለመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ቡድኑ ከፊት በሚፈለገው መጠን ስል አለመሆኑ እና በቂ የጐል እድሎችን አለማግኘቱን እንዲሁም የሳዲቅ ሴቾን የ2ኛና 16ኛ ደቂቃ ጐሎች መስተናገዱን ተከትሎ ሳሙኤል ሳኑሚን የዳዊት ፍቃዱ ጋር ከፊት በማጣመር እና ብርሃኑ ቦጋለን በጨዋታው መጀመሪያ ከነበረበት ቦታ በግራ በኩል ወደፊት ገፍቶ እንዲጫወት በማድረግ እንዲሁም ያሬድ ዝናቡን በመጀመሪያው አጋማሽ በቀሩት 15 ደቂቃዎች እንዲሁም እሱን ተክቶ የገባውን ሄኖክ ካሳሁንን በሁለተኛው አጋማሽ በብቸኛ የተከላካይ አማካይነት ሚና በመጠቀም ቡድኑን ወደ 4-1-3-2 የቀረበ አጨዋወትን ይዞ የጨዋታውን ቀሪ 60 ደቂቃዎች እንዲጨርስ አድርጐታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና የመሀል ሜዳ የበላይነት
ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ለሙሉ የበላይነቱን በወሰደበት የትላንት ምሽቱ ጨዋታ የቡድኑ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ለውጤቱ ማማር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ የቡድኑ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች በማጥቃት ጊዜ የሜዳውን መጨቅየት በመቋቋም በቁጥር የበዙ የተሳኩ የኳስ ቅብብሎችን ለማድረግ ችለዋል፡፡ በደደቢት የተከላከይ አማካይ እና ተከላካዮች መካከል ይፈጠር የነበረውን ክፍተት ተከትሎ አብዛኛው የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር በደደቢት የግብ ክልል የቀረበ እና በሁለቱ መስመሮች የነበረውን ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያማከለ በመሆኑ የኳስ ቁጥጥሩ ኳስን ከመያዝ ባለፈ የግብ እድሎችን በብዛት ለመፍጠር የሚያግዝ አይነት ነበር፡፡ በተለይ የመስዑድ እና የኤልያስ እንቅስቃሴ ለዚህ ስኬት ቁልፍ ነበር፡፡ ተጨዋቾች ከኋላ የሚቀበሏቸውን ኳሶች ከመስመር አማካዮቹ ጋር በመቀራረብ እና በተሳካ ሁኔታ በመቀባበል እንዲሁም ሰፋ ባለ እይታ ኳሱን በፍጥነት ወደ ሁለቱ መስመሮች በመጣል ኳስ በያዙ ቁጥር ለተጋጣሚያቸው በቀላሉ የማይተነበይ ዓይነት ተለዋዋጭ ውሳኔዎችን በመወሰን ቡድናቸው የመሀል ሜዳ የበላይነቱን እንዲወስድ አድርገውታል፡፡ የሁለቱ ተጨዋቾች በተለያዩ አጋጣሚዎች በመናበብ እና ቦታ በመቀያየር ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴም ሌላው በተጋጣሚያቸው ዘንድ ተገማች እንዳይሆኑ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡
ከመስዑድ እና ከኤልያስ በተጨማሪ በመሀል ሜዳው ግራ እና ቀኝ መስመር የአማኑኤል እና የእያሱም እንቅስቃሴም አስገራሚ ነበር፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች በማጥቃት እና በመከላከል ወቅት የነበራቸውን ሚና ይወጡ የነበረበት መንገድ ሌላው የአማካይ መስመሩ ጥነካሬ አድርጓቸው አምሽቷል፡፡ ተጨዋቾቹ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ከመሀል አማካዮቹ የሚቀበሏቸውን ኳሶች ወደውስጥ ይዞ በመግባትም ሆነ ከፊት አጥቂው ከሳዲቅ ጋር እና ከመስመር ተከላካዮቹ ጋር ያደርጓቸው በነበሩ የተሳኩ ቅብብሎች አማካይነት አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውለዋል ፡፡ በተለይም የሁለቱ ተጨዋቾች የተመጣጠነ አቀራረብ ቡድኑ አንዱን መስመር ብቻ ይዞ በማጥቃት ተገማች እንዳይሆን አጠቃቁ በሁለቱም መስመሮች ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና አማካይ መስመር በሽግግሮችም ወቅት ከተጋጣሚው ልቆ ታይቷል፡፡ ቡድኑ ኳስ ሲነጠቅ በፍጥነት የመከላከል ቅርፁን በመያዝ በተለይም የደደቢትን የመስመር አጨዋወት ፈጥኖ በመዝጋት ተጋጣሚያውን ሙሉ ለሙሉ ወደ መሀል እንዲጠብ በማድረግ በኩል የተሳካላቸው ነበሩ፡፡
በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ ይፈጠር የነበረውን ክፍተት በመዝጋትም በኩል የአማካዮቹ የመናበብ ሂደት የተዋጣለት ነበር፡፡ ይህም ቡድኑ በመከላከሉ ብዙ እንዳይቸገር እና እንዲሁም የተከላከይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም ኳስ የማጨናገፍ እና የመመስረት ስራውን በነጻነት እንዲወጣ ረድቶታል፡፡ ከዚህ በተለየ ቡድኑ ወደማጥቃት ያደርግ የነበረውም ሽግግር ከአደገኛው የመስመር አጨዋወቱ ጋር ተዋህዶ በተጋጣሚው ላይ ድንገተኛ የሆኑ ማጥቃቶችን እንዲሰነዝር ረድቶታል፡፡ በነዚህም ፈጣን እንቅስቃሴዎች አማካይነት ከደደቢት ተከላካዮች ጀርባ ለሳዲቅ ሴቾ ጥሩ የሚባሉ የግብ አጋጣሚዎችንም ፈጥረውለት ነበር፡፡
የቡድኑ የመሀል ሜዳ የበላይነት በጨዋታው ከታየው ድንቅ የመስመር የማጥቃት አካሄድ ጋር ተደምሮ ከተጋጣሚው ተከላካዮች መሀል ሆኖ ኳስ የመቀበያና የመሮጫ ክፍተትን ይፈጥር የነበረው ሳዲቅ ሴቾም ያገኛቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ በመቀየሩ በኩል ተሳክቶለት አምሽቷል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ መስመር ጨዋታውን በተፈለገው መንገድ በማስኬድ ለወጤቱ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል፡፡
አብዱል ከሪም መሀመድ እና አህመድ ረሺድ
በዘመናዊ እግር ኳስ እጅግ ወሳኝ እየሆኑ ከመጡ የተጨዋቾች ቦታዎች እና ሚናዎች መካከል የመስመር ተከላካዮች ሚና እንዱ ነው፡፡ አራት የኋላ መስመር ተሰላፊዎችን የሚጠቀሙ ቡድኖች ላይ ከመሀል ተከላካዮች ጎንና ጎን ስለሚገኙ የመስመር ተከላካዮች እንበላቸው እንጂ በዘመኑ እግር ኳስ ስኬታማ በሆኑ ቡድኖች ላይ የምንመለከታቸው የዚህ ቦታ ተጨዋቾች በማጥቃት ላይ ያላቸው ሚና ከመከላከሉ ይልቅ ከፍ ያለ ነው፡፡
በተለይ በትልቅ ደረጃ በቦታው የተሳካላቸው የሚባሉት ተጨዋቾች የጨዋታው አብዛኛው ክፍል እንቅስቃሴያቸው በተጋጣማያቸው ሜዳ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ በመሆኑም ቡድናቸው የሜዳውን የጐን ስፋት በሚገባ እንዲጠቀም፣ የመሀል አማካዮችም ኳስ የማቀበያ አማራጮች እንዲበዙላቸው የፊት አጥቂዎችም ከተጋጣሚ ተከላካዮች የሚደርስባቸውን ጫና እንዲቀንስ ለማድረግ የነዚህ ተጨዋቾች ሚና ወሳኝ ነው፡፡
ነገር ግን በሀገራችን እግር ኳስ የመስመር ተከላካዮች ማጥቃት ላይ ያላቸው ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በክለቦቻችን እና በብሔራዊ ቡድኖቻችን ላይም አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የመስመር ተከላካዮቻችን ሚና በአመዛኙ በመከላከል ላይ የተገደበ ነው፡፡
የትላንትናው የኢትዮጵያ ቡና የግራና የቀኝ የመስመር ተከላካዮች አህመድ ረሺድና አብዱልከሪም መሀመድ እንቅስቃሴ ግን በቦታው ላይ በቡድኑ አዲስ ዓይነት ምዕራፍ እየተከፈተ እንደሆነ እና ሌሎቹም ቡድኖች ብዙ ሊማሩበት እንደሚገባ ያመላከተ ነበር፡፡ የሁለቱ ተጨዋቾች የማጥቃት ተሳትፎ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የነበረ ቢሆንም የትላንቱ ጨዋታ ላይ የነበራቸው አቀራረብ ግን የቡድኑ ውጤት ዋነኛ መነሻዎች አድርጓቸው ነበር፡፡ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመሄድ ከኋላ ክፍተት ከተዉባቸው አጋጣሚዎች ውጪ እንደቡድኑ የማጥቃት አቅጣጫ አንዳቸው ወደፊት እስከ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ድረስ በመሄድ ማጥቃቱን ሲያግዙ አንዳቸው ከመሀል ተከላካዮቹ ብዙም ሳይርቁ ቡድኑን ከመልሶ ማጥቃት ለመከላከል በተገቢው ቦታ ላይ ይገኙ ነበር፡፡ ኳስ በራሳቸው ሜዳ ላይ በተቃራኒ አቅጣጫ በመመስረት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ላይ በሌላኛው መስመር (ለምሳሌ ኳስ በግራ በኩል እየተመሰረተ ከሆነ በቀኝ በኩል ባለው ክፍተት እንደማለት ነው) የሚኖረውን ክፍተት በመጠቀም በፈጣን ሩጫ ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ ሲገቡ ከላይ የተጠቀሱትን ከመስመር ተከላካዮች የሚገኙ ጥቅሞችን በሙሉ ለቡድናቸው ሲሰጡ ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴያቸው ተጋጣሚያቸው በተጨዋቾች መካከል የሚኖረውን ርቀት መመጠን እንዳይችል እና የቡድናቸው የአማካይ መስመር ኳስ የማንሸራሸሪያ ቦታ እንዲያገኝ በማድረጉ በኩል የሰሩት ስራ ለቡድኑ የመሀል ሜዳ የበላይነት እና የመሀል አማካዮቹ ለነበራቸው ነፃነት ወሳኝ የሆነ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል፡፡
የደደቢት ወደ መሀል የጠበበ አጨዋወት
በተጋጣሚው በእጅጉ ብልጫ የተወሰደበት የደደቢት የመሀል ክፍል ቡድኑ ከተቆጠሩበት የመጀመሪያ ደቂቃ ጐሎች ጋር ተዳምሮ ደደቢቶች ጨዋታው እንዲከብዳቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በጨዋታው መጀመሪያ በአንድ አጥቂ ተጠቅሞ የመሀል ሜዳውን ብልጫ በቁጥር ለመስተካከል በአምስት አማካዮች የተጠቀመው ደደቢት በተጋጣሚዎቹ የመስመር ተከላካዮች እና የመሀል አማካዮች እንቅስቃሴ ምክንያት ያሰበውን ማሳካት አልቻለም፡፡ በተለይም በቀኝ በሳሙኤል ሳኑሚ በኩል በጨዋታው መጀመሪያ ላይ በረጅሙ ይጣሉ የነበሩ ኳሶችም የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም ነበር፡፡ ቡድኑ የጨዋታ ቅርፅ ማስተካከያም ካደረገ በኋላ ከፊት የአጥቂዎቹን ቁጥር ወደሁለት በማሳደጉ አልፎ አልፎ ይገኙ የነበሩ እድሎችን ወደጐል ለመሞከር ያስቻለው የነበረ ቢሆንም ወደመሀል በጣም የጠበበ የነበረው አቀራረቡ በታሰበው መንገድ የበላይነት ሊሰጠው አልቻለም፡፡
ደደቢት ወደ 4-1-3-2 ቅርፅ ከመጣ በኋላም እንደመጀመሪያው ጊዜ ሁሉ በተለይ ከሳምሶን ግራና ቀኝ የነበሩት የሽመክትና የብርሀኑ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ወደ መሀል የጠበበ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በመስመሩ ጠንካራ ከነበረው የተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ ምክንያት የተፈጠረ ሊሆን ቢችልም ቢያንስ በአንደኛው መስመር በኩል እንኳን በመጠኑ የተለጠጠ የማጥቃት አማራጭ ለመከተል አልቻሉም ነበር፡፡ የቡድኑ ፈጣሪ አማካይ ሳመሶን ጥላሁንም ኳስ የማደራጀት ሚናውን ለመወጣትም ሆነ የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች በሚፈለገው መጠን ለማድረስ በቂ ክፍተት ማግኘት ተቸግሮ ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋቾች በቁጥር አንሰው ኳስ ከመሀል ሜዳው በጥቂቱ ወደ ቡና የግብ ክልል ውስጥ በምትሆንበት ሰዓት እንኳን ደደቢቶች የሜዳውን ስፋት ተጠቅመው ከተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት ያደርጉት የነበረው ጥረት እምብዛም ነበር፡፡ ቡድኑ ይህንን ችግሩን ለመቅረፍ የተጨዋች ቅያሬም ያደረገው በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ነበር፡፡ ብርሀኑ ቦጋለን ወደ መስመር አማካይነት በመመለስና ጆሴፍ አግዮኪን ወደ ሜዳ በማስገባት በቀኝ መስመር በኩል የማጥቃት መስመሩን ለማስፋት በማሰብ የተደረገው ይህ ቅያሬም ለውጥ ለማምጣት በቂ ጊዜ ሳያገኝ ጨዋታውን በ3-0 ሽንፈት ለማጠናቀቅ ተገዷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ቀጥለው ሲካሄዱ በመጪው ረቡዕ በ9፡00 ደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲገጥም ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭ ከተማን በ10:00 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚያስተናገድ የፌዴሬሽኑ መርሀ ግብር ያሳያል፡፡