የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሩዋንዳ የእግርኳስ ውድድር እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቦለታል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 10 ጀምሮ በኪጋሊ በሚደረገው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሰለባዎች መታሰቢያ የእግር ኳስ ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቦለታል። ሩዋንዳ በውድድሩ እንዲሳተፉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ6 የአፍሪካ ሃገራት ወጣት ቡድኖች ግብዣውን የላከች ሲሆን እነዚህም ጋቦን፣ ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮትዲቯር እና ሞሮኮ ናቸው።

ሩዋንዳ እ.ኤ.አ. በ1994 በሃገሪቱ በነበረው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሰለባ የነበሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ዜጎችን ለማሰብ የምታዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ባለፈው ዓመት ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያን ተሳታፊ አድርጓል።

በአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር ከጋና አቻው ጋር በመጪው እሁድ የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን በዝግጅት ላይ ይገኛል። ቡድኑ ጋናን ማሸነፍ ከቻለ በሰኔ ወር መጨረሻ ከቱኒዚያ እና ሴኔጋል አሸናፊ ጋር ለሚያደርገው የመጨረሻ ዙር ጨዋታ የሩዋንዳውን ውድድር እንደመዘጋጃ የወዳጅነት ጨዋታ መጠቀም የሚችል ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *